ስለ መጽሐፉ አስተያየት

ነሐሴ 7 ቀን 2009 ዓ.ም

ይድረስ ለክብርት ዶ/ር ስንታየሁ ካሣ

ጉዳዩ፡ካሣ ገብረማርያም በሚል ርዕስ ስለጻፍሽው መጻሕፍ አጭር አስተያየት

በቅድሚያ የተከበረ ሰላምታ አቀርባለሁ፡፡ በአገራችን ባህል ሆነ ልምድ የማያውቁትን ሰው አንቱ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ሆኖም፤ ከመጽሐፍሽ እንደተረዳሁት በዕድሜ ስለምበልጥሽ የሹመት/የሥልጣን ግዴታ ከሌለ በስተቀር በባህላችን መሠረት አንቺ እንድል ይፈቀድልኝ፡፡

መጽሐፉን ያነበብኩት ጓደኛየ መጽሐፉን አንብቦ በአባትሽ ታሪክ እና በአንችም ጥረት ተመስጦ ማንበብ እንዳለብኝ በመገፋፋቱ ብቻ ሳይሆን፤ ታሪኩንም በሙሉ ባይሆን አስኳል አስኳሉን ለእኔና ለሌሎች ጓደኞቻችን በስሜት ስለአንችም ስለአባትሽም በመግለጽ በል አንብ ብሎ መጽሐፉን ሰጥቶኝ ነው፡፡ ገዝተህ አንብብ እንኳ አላለኝም፡፡ መጸሐፉን እንዳነብ ፍላጎቱ ሆነና ተቀብየ አነበብኩት፡፡

እኔም መጽሐፉን እያነበብኩና ከጨረስኩ በኋላም እንደጓደኛየ በስሜት ውስጥ ገባሁ፡፡ በሁለት ነገሮች ስሜቴ ተነካ፡፡ አንደኛው የአባትሽ የጀግንነት ታሪክ ሲሆን፤ ሁለተኛው ከአብራካቸው የተገኘሽ የልጃቸው የአንች ልፋት፤ የማወቅ ጉጉት፤ እልህ፤ቁጭት፤ጥረትና የዓለማ ቆራጥነት ነው፡፡ ተገረምኩ፤ ተደነቅሁም፡፡ በአጭሩ ከመጽሐፉ ተነስቼ በሚከተሉት አራት ፍሬ ሀሳቦች ላይ አስተያየቴን ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡

  1. ልጅ የአባት ማንነት ማሳያ መሆን – ታሪካቸው ተቀብሮ እንዳይቀር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የአባትሽን የኮ/ል ካሣ ገብረማርያምን አስተዳደግ፤ ትምህርትና ወታደራዊ ተልዕኮ በሰፊው አቅርበሽልናል፡፡ ስለመልካም ባህሪያቸው፤ በሙያቸውና በሥራቸው የተመሰገኑና የተከበሩ፤በዓለማ ጥንካሬያቸው እና በጀግንነታቸው የታወቁ መሆናቸውን ከመጽሐፍሽ ተረድቻለሁ፡፡ብዙ ጊዜ ጠንካራ ወላጆች እንደራሳቸው ጠንካራ ልጆች ለመተካት ሳይታደሉ ሲቀር የእሳት ልጅ አመድይባላል፡፡ ይህ አባባል በአንቺ ላይ የማይሠራ ሁኖ ተገኝቷል፡፡ እንዲያውም፤ ስለአባትሽ ያለሽ ፍቅር፤ታሪካቸው ተዳፍኖ እንዳይቀር ያደረግሽው እልህ አስጨራሽ ሥራ እውነትም ኮ/ል ካሣ ጀግና ነበሩ ማለት ብቻ ሳይሆን አንችም ጀግና ነሽ ያሰኛል፡፡ ከጀግና ጀግና ይወለዳልና በጀግንነትሽ በጥረትሽ የአባትሽን ጀግንነት አሳይተሻል፡፡ ስለሆነም፤ በአባትሽ ብቻ ሳይሆን፤ በራስሽም ልትኮሪና የመንፈስ እርካት ልታገኝ ይገባል፡፡
  1. የኮ/ ካሣ ገብረማርያም ጀግንነት – መጽሐፍሽ በርዕሱና በይዘቱ ስለኮ/ል ካሣ ይተርክ እንጂ ታሪኩ የሚያጠነጥነው ስለኮ/ል ካሣ ብቻ ሳይሆን፤ ኮ/ል ካሣን የመሰሉ የኢትዮጵያ አኩሪ ልጆቿን ጭምር የሚመለከት የአገር ታሪክ ነው፡፡ አገራችን የበርካታ የቁርጥ ልጆች እና የጀግኖች እንዲሁም በተቃራኒው የበርካታ ባንዳዎች፤ የእናት ጡት ነካሾች አገር ነች፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ የአርበኞችና የባንዳዎች፤የጀግኖችና የፈሪዎች እናት ናት፡፡ታዲያ የኢትዮጵያ ልጅ ኮ/ል ካሣ ገብረማርያም በደግ ሥራቸው፤ ለእናት አገራቸው በበርሃ ሲፋለሙ ደማቸውን አፍስሰው፤ አጥንታቸውን ከስክሰው ውድና የማይተካ ህይወታቸውን መስዋዕት ያደረጉ ከውድ ልጆቿ የሚሰለፉ ባለታሪክ ናቸው፡፡ እንደሳቸው ያሉ ከከፍተኛ አመራር እስከታች ተራ ወታደር ድረስ ሲፋለሙ የወደቁ ለጠላት እጅ አንሰጥም በማለት ውድ ህይወታቸውን በወኔና በክብር በእራሳቸው ሽጉጥ፤ ቦንብ ወይም በመሰላቸው ዘዴ በበርሃ በአቀበት ቁልቁለት፤ በዱር በገደል በአሸዋማ በድንጋያማ ሜዳ በሸለቆ፤ በወንዝ ሸንተረሩ እራሳቸውን ያጠፉ፤ በቀይ ባህር የሰጠሙ በርካታ ናቸው፡፡ ኮ/ል ካሣ ከከበባ ማምለጫ መንገድ ሳያጡ ጦራቸውን ሳይክዱ ከወገናቸው ጋር በረሃ የቀሩ አዋጊና ተዋጊ የነበሩ ምንጊዜም ታሪክ የማይረሳቸው ጀግና ናቸው፡፡ በእርሳቸው የጀግንነት ታሪክ መጽሐፍሽ የሌሎችንም የጅግንነት ታሪክ በዓይነ ልቦና እንድናይ አስችሏል፡፡
  1. ለምስክርነት ስለቀረቡት – ስለአባትሽ ማንነት በቃለ ምልልስ ፤ ከሰነዶች እና ከመጻሕፍት ለማግኘት ያደረግሽው ጥረት ግሩም ድንቅ የሚያሰኝ ነው፡፡ በአንድ ሁለት ሦስት ሳትወሰኝ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎችን ማናገርሽ ጥንካሬሽን ያሳያል፡፡ በስደት እና በአገር ውስጥ 87 ወታደራዊ መኮንኖች የነበሩ (30 ጄኔራል መኮንኖች- በአገር ውስጥ 19 እና በስደት 11 እንዲሁም 41 ከፍተኛ መኮንኖች- በስደት 8 ኮሌኔሎች እና 8 ሻለቆች እና በአገር ውስጥ 23 ኮሌኔሎች እና 4 ሻለቆች እና 14 መስመራዊ መኮንኖች- በስደት 5 ሻምበሎች እና በአገር ውስጥ 5 ሻምበሎችና 4 መቶ አለቆች) እና ከወታደራዊ መስክ ውጭ በመንግሥት ሠራተኝነት ተሰማርተው የነበሩ 14 ሲቪሎች በጠቅላላ 101 ለምስክርነት አነጋግረሻል:: ካንዳንዶች መጣጠፎቻቸውም አጣቅሰሻል፡፡ ድንቅ ሥራ፡፡

በምስክርነት የቀረቡትን ሃሳቦችና አስተያየቶች ስመለከት፤ በወታደራዊ መስክ ያጋጠሙ ችግሮችን በተመለከተ ከተለያዩ ምንጮች ያነበብናቸውና የሰማናቸው ጎላ ብለው ተንጸባርቀዋል፡፡ ለአገሪቷ ወታደራዊ ፍልሚያ ውድቀት ከሚነሱት ምክንያቶች መካከል፤የወታደራዊ ዕድገት በአብሮ አደግነት፤በትምህርት ቤት ጓደኝነት፤ በዝምድና የተተበተበና ቅጥ ያጣ የዕዝ ሰንሰለት የሰፈነበት፤ በወሳኝ የትግል ፍልሚያ ሜዳዎች የወገን ጦር ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ የያዘውን ገዥ ቦታ አላግባብ እንዲለቅ የሚታዘዝበት፤ አጠገቡ ያለ የወገን ጦር በዕድገት ማጣት ማኩረፍ ወይም በግል ጥላቻ ለዕርዳታ የማይቀርብበት ሁኔታ የሚከሰትበት፤በሶቭየት ሕብረት እና በኢትዮጵያውያኑ ጄኔራሎችም የተሳሳተና ደካማ መመሪያ የሚሰጥበት፤ጦሩ ስንቅና ትጥቅ አልቆበት በቀላሉ የሚመታበት፤ ወታደሩ የሚልሰው የሚቀምሰው ምግብ ፤ጉሮሮውን የሚያርስበት ውሃ አጥቶ ልብሱ ከነመጫሚያው በላዩ አልቆ የሚለውጠው አጥቶ፤ህክምና እርቆት በርሃብና በውሃ ጥም በዕርዛትና በበሽታ የሚሰቃይበትና በቀላሉ በጠላት ወገን የሚፈታበት፤የጦር መሪዎች አንዳንዶቹ በተስፋ መቁረጥ ወይም በውስጥ ሴራ ግዴለሽነት ያሳዩበት እንዲህና እንዲያም ሁኖ የጦር መሪዎች ከከፍተኛ እስከመጨረሻ የአመራር እርከን የተሰለፉ መኮንኖች፤ባለሌላ ማዕረጎች እና ወታደሮች ሙስናውንና ድክመቱን ወደኋላ ትተው የሕይወት መሳዋዕትነት የከፈሉበት፤አንዳንዶቹ ደግሞ በጥቅም በመታወር ለጠላት ወገን የተሰለፉበት፤የአንዳነድ አየር ኃይል ተልዕኮ ዒላማውን ስቶ ሳይሆን ሆን ብሎ ቦንቡን ድንጋይ ላይና ባህር ውስጥ ጥሎ የሚመለስበት፤የጠላት ወገን የውጊያ ስልቱንና ዕቅዱን በቀላሉ የሚያገኝበት ዝብርቅርቅ ሁኔታ የታየበትና የሁሉም ድምር የአገር ሽንፈትና ውርደት የደረሰበት፤ለአገራቸውና ለወገናቸው ራሳቸውን መስዋዕት ያደረጉትን እንኳ በቅጡ ባለውለታነታቸው ያልታወቀበት የሞት ሞት ታሪክ የወረስንበት ሁኔታ ገሃድ ሆነ፡፡ የኮ/ል ካሣና መሰሎቻቸው በማዕረግ ሳይከለል ለኢትዮጵያ አንድነትና ልዑዓላዊነት መከበር የተሰው ጀግኖች ታሪክ በዚህ የተተበተበ ታሪክ ውስጥ መገኘቱ የግድ ነው፡፡ የምስክሮችሽ ዕይታም በአጠቃላይ ከዚህ ውጭ የሆነ አይደለም፡፡

ለምስክርነት ያቀረብሻቸው ሁሉም ስለኮ/ል ካሣ ገብረማርያም ተመሳሳይ ቃል መስጠታቸው ስለእርሳቸው ያለሽን እምነትና ስለአወዳደቃቸው ላደረግሽው እውነትን ፍለጋ በቂና አስተማማኝ ማረጋገጫ የሚሆን ነው፡፡ ሆኖም ግን፤ ለምስክርነት ያቀረብሻቸው ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉ ጠንካራ እና የተመሰከረላቸው ጀግኖች የመኖራቸውን ያህል ለምስክርነት ሊበቁ የማይችሉም አይጠፉም ማለት ይቻላል፡፡ ይህን ለማለት ያበቃኝ ምክንያት አንዳንዶቹን በቅርብ ሆነ በቅርብ ርቀት የማውቃቸውን ያህል ብዙም ሚዛን የማይደፉ ስለሆኑ እና የማላውቃቸው ያንዳንዶች አባባል ደግሞ እንዲሁ በአገራዊ ጉዳይ ላይ ለምስክርነት ይበቁ አይበቁ አጠያያቂ ስለሆኑብኝ ነው፡፡

ይህ አመለካከት እንደተጠበቀ ሁኖ፤ አሁንም የማያውቁትን እንደሚያውቁ አድርጎ ለመገኘት የመሞከር፤ችግሮች ከአጠቃላዩ ሥርዓት መሆኑንና እነርሱም በሥርዓቱ ተጠያቂ ሁነው ሳለ ከደሙ ንፁህ እንደሆኑ በማስመሰል በግለሰቦች ላይ ጣት መቀሰር ብቻ የታየበት ትናንት ለጠፋው አሁንም ራስን ከታሪክ ተጠያቂነት አድኖ ለመገኘት የመጣርና በፊትም የነበራቸው በሽታ በስደትም ይሁን በአገር ውስጥ ለግል እንጂ ለአገር ያለማሰብ የቆሙ መሆናቸውን፤ ለአገሪቱ መሪ ዋና ታማኝና አቀንቃኝ እንዳልነበሩ እና ለኮ/ል ካሣ ሆነ ለሌሎች ተመሳሳይ ወገኖች ውድቀት እና ብሎም ለአገር ውድቀት በጋራና በተናጠል ተጠያቂ እንዳልሆኑ ሁሉ ሲናገሩ፤መረጃ ከዚህና ከዚያ አገኘን እያሉ ምን አደረጋችሁ ለሚባል መልስ መስጠት የማይችሉ፤ ሌላውን ከማንቋሸሽ ውጭ ከጠላት ወገን ጥንካሬና ደካማ አንጻር በእራስ መዋቅር ውስጥ በሰርጎገብነት ሲሠራ ስለነበረው ሁኔታ በመረጃም ይሁን በትንታኔ ማቅረብ ያለመቻሉ፤ የእከሌ ወገን፤ የእከሌ የትምህርት ቤት ጓደኛ ወ.ዘ.ተ እየተባለ የትምህርት ደረጃንና የሥራ ልምድ ችግርን ከተሰለፈባቸው የጠላት ወገን አንጻር መመልከት ያለመቻል፤ መሪውን ያልሆነውን ነህ እያሉ ሊያወርዱት በማይችሉበት ቦታ ከሰቀሉና እዚህ ካደረሱ በኋላ ከደሙ ንፁህ እንደሆኑ በመታከት አሁንም ትናንት በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ የተጠናወታቸው በሽታ የርካሽ ፐሮፓጋንዳ አባዜ ምን ያህል እንዳልጸዳ መጽሐፍሽ ጥሩ መስታወት ሁኗል ማለት ይቻላል፡፡

የአንዳንዶችን አባባል ለመጥቀስ ያህል- ኮ/ል ካሣ ከነበራቸው የአመራር ብቃትና ችሎታ በመነሳት እዚያ የተሰውበት ቦታ መላክ አልነበረባቸውም፤ በእርሳቸው ማዕረግ እዚያ ጦር ቦታ መገኘት አልነበረባቸውም፡፡ መሞት አልነበረባቸውም የሚል ይገኝበታል፡፡ ይህ አባባል አነጋጋሪ ነው፡፡ ብዙም ያስኬዳል፡፡ አዛኝ ቅቤ አንጓች እንዲሉ በመርዝ የተለበሰ ማር አቀራረብ ይመስላል፡፡ በአንድ በኩል ደካማ ሲላክ ያን ደካማ መላክ ባልተገባ ነበር ይባላል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ጠንካራ ሲላክ ለማስገደል ሆን ተብሎ ነው ይባላል፡፡ ግራ የሚያጋባ ውስብስብ ነገር፡፡ በእርግጥ አባባሉ እንዳንዴ እውነትነት አለው ሊባል ቢቻልም በማስረጃ ባልተደገፈ መልኩ አጠንክሮ ማቅረቡ አግባብነት ሊፈተሸ የሚገባ ነው፡፡ ለነግሩማ እንኳንስ በወታደሩ ይቅርና በሲቪሉ የዘመቻ ምልመላ በየቦታው የነበሩ ካድሬዎች ከየመ/በቱ እየመለመሉ ይልኩ የነበሩ አንድም በሥልጣን ሽሚያው የሚፈሩትን አልያም የሚጠሉትንና ከእነርሱ አስተሳሰብ ወይም ቡድን አልቆመም ብለው የሚያምኑበትን እንደነበር በብዙ ቦታ ሁካታን፤ ጫጫታንና ጭሆትን አስከትሏል፡፡ በተጨባጭም ተስተውሏል፡፡ ታዲያ ይህ እውነታ ቢኖርም በከፍተኛ ደረጃ ለሚሰጥ ወታደራዊ ተልዕኮ ላይ የሚሰጥ አስተያየት ግን ከተራ አሉባልታ ወጣ እንዲል ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡

ያን ጊዜ በሥልጣን ሹክቻ ግለሰቦችን ለማስጠፋት ሲባል ሆን ተብሎ ከነሠራዊታቸው ለመጥፎ ቦታና ለሞት ይዳረጉ ነበር ማለት ምን ያህል ፀያፍ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ከግለሰቡ ጋር ሌላው ሁሉ አብሮ እንዲደመሰስ የመፈለግ ዕቅድ እንደነበር ማሰብ ምነኛ ከባድ ነው፡፡በጠላት ሴራና በውስጥ ከሃዲ መሣሪያነት ሊኖር እንደሚችል መገመት አንድ ነገር ነው፡፡ ግን፤ከዚያ ውጭ በግለሰብ ደረጃ ይደረግ ነበር ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ አንድን መሪ በተለያዩ ዘዴዎች ማስወገድ እየተቻለ ለምን ከሠራዊቱ ጋር በፍራቻ ወይም በጥላች ብቻውን ሳይሆን ከወገን ጋር እንዲጠፋ ሆን ተብሎ ይደረጋል? በሰርጎገብነት የገባ የጠላት የውስጥ አርበኛ አያደርግም አይባልም፡፡ በዚህ ባለተፈረጀ ሰው ግን እንዴት ሊሆን ይችላል? ለማመን በጣም ይከብዳል፡፡

ከሆነም፤በእንደነዚህ ዓይነት መስካሪ ወታደራዊ አመራሮች ነው እንግዲህ አላስፈላጊ መስዋዕትነት የተከፈለውና አገር ለዚህ የበቃችው፡፡ብዙ የጦር ሜዳዎች በእርስ በርስ ሽኩቻ በመጠላለፍ እና በእኩይ ሴራ ወገን ተሰውቷል፡፡በስህተትም ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ደርሷል፡፡ ስህተት አልተሠራም አይባልም፡፡ አውቆ ሆን ተብሎ ከተደረገ የጥፋት ጥፋት አስከፊና አስፈሪ እኩይ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአንዳንዶችን አባባል ለመቀበል ምን ያህል እንደከበደሽ እና በጭፍን አስተያየታቸውን መቀበል እንዳቃተሸ ከራስሽ ህሊና መሟገትሽን ሳይ እውነትም ስንታየሁ የእኒህ ኩሩ ጀግና ልጅ ናት የሚያሰኝ የአባትሽን ሥነ ምግባርና ጀግንነት የምታንጸባርቂ መሆንሽ ውል ብሎ ታይቶኛል ስል በማጋነን አይደለም፡፡

ከላይ ለመጠቆም እንደሞከርኩት ከጠንካራ መስካሪዎች በተጨማሪ በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በተለያየ ደረጃ ለአገራችን ውድቀት አሉታዊ አስተዋጽኦ ያደረጉትንም መጠየቅሽ አልቀረም፡፡ይህም ባልከፋ፡፡ ግን መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር፤ በአገራችን የጥፋት ቡኮ እንዳላቦኩ ስለእነኮ/ል ካሣ ዓይነቱ ምስክርነት ለመስጠት የሞራል ብቃታቸው አጠያያቂ መሆኑ ነው፡፡ መጽሐፍሽ ለአገራችን ውድቀት ምስክርነታቸውን ከሰጡ መካከል እራሳቸው ምንም ሳይሠሩ በሌላው ላይ ጣት ሲያስቀስሩና ሲቀስሩ የኖሩና አሁንም ያው የጥፋት አባዚያቸው ያለቀቃቸው መኖራቸውን ማሽተት ብቻ ሳይሆን በሚገባ መገንዘብ አስችሏል፡፡ በቃለ መጠይቁ አጋጣሚ ጀግና በማወደስ ስም እራሳቸውን ያሞካሹ የመሰላቸው አልጠፉም፡፡ እናም የጀግና መስካሪ ሊሆኑ እንደማይችሉ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይልቁንስ፤ሞክረሽ ማግኘት ተስኖሽ ሊሆን ይችል ይሆናል እንጂ ለምስክርነት ከኮ/ል ካሣ ጋር የተሰለፉ የበታች ሹማምንት ወይም ባለሌላ ማዕረጎች እና ተራ ወታደሮችን ምንም እንኳ አብዛኞቹ በጦር ሜዳ የተሰው ቢሆኑም፤ ከተረፉት መካከል በጣት የሚቆጠሩትን ቃለ መጠይቅ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ቢኖርሽ ኖሮ ደግሞ እንዴት ጥሩ ነበር ለማለት እደፍራለሁ፡፡

ከመስካሪዎች አባባል በጣም ብዙ ትምህርት ይገኛል፡፡ የመሰከሩት ስለ ኮ/ል ካሣ ብቻ አይደለም፡፡ ኮ/ል ካሣን በመሰሉ፤ በእራሳቸው እና ብሎም በአገሪቷ ስለተሠራው ቀውስና ደባ ምን ያህል የአመራርና የአመለካከት ድህነት ተንሰራፍቶ እንደነበርና አሁንም ችግሩ ያለመትነኑን ጭምር ነው፡፡ ከሰጡሽ ምስክርነት በመነሳት ብዙ፤ በጣም ብዙ መተንተን የሚያስችል ለምርምር ከፍተኛ ግብዓት የሚሆን ሥራ ነው የሠራሽው፡፡

  1. ከኮ/ ካሣ አቋም የተወሰደ አገራዊ ፋይዳ በትረካው ውስጥ ኮ/ል ካሣ ለወታደራዊ ሙያቸው እና ግዴታቸው እንጂ ለፖለቲካና ለሥልጣን ስስት እንደሌላቸው ነው፡፡ እጅግ በጣም የሚደነቅ አቋም ነው፡፡ የአገራችን ውድቀት አንደኛውና ዋናው ምክንያት በወታደሩ ሆነ በሲቪሉ የሥራ መስክ ያለሙያው፤ ያለብቃቱ፤ ያለችሎታው፤ያለአቅሙ፤ያለልምዱ በተለይ ወታደራዊ አመራር ካለባህሪይው የፖለቲካ ሥልጣኑን ሙጭጭ ብሎ ይዞ ለ17 ዓመታት በተወላገደ ሃዲድ ተጉዞ መጨረሻ አገርን ለጥፋት መዳረጉ ነው፡፡ ውጤቱ ካለዝርዝር ሀተታ አገሪቷ ያለችበት ሁኔታ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ የጀግኖችን መስዋዕትነት ከንቱ ያደረገ ነው፡፡ ሁሉም በሙያው እና በሚመጥነው ቦታ ቢሰለፍ ኖሮ የነበረው ድንብርብር እና ውዥንብር ብሎም አስከፊ ውድቀት ባልተፈጠረ ነበር፡፡

ለማጠቃለል፤ ዶ/ር ስንታየሁ እንደስምሽ ስንት ሥራ ሠርተሻል፡፡ ሥራሽ ግን ግለሰባዊ ብቻ ሳይሆን አገራዊ ታሪክ ስለሆነ ልትመሰገኝ ይገባል፡፡ አባትሽ በ1969ዓ.ም የገነት ጦር ት/ቤት አዛዥ ሆነው ለዕጩ መኮንን ምሩቃን ካደረጉት ንግግር ውስጥ ያስቀመጥሽው ታሪክ እኛንም እናንተንም በሕሊና መነጽሯ እየተመለከተች ነው፡፡ የምትመሰክርልን እንጂ የማትመሰክርብን እንዲሆን እመኛለሁ ያሉት መሪ ቃል ግሩም አባባል ነው፡፡ አዎ! ታሪክ ለኮ/ል ካሣ መስክራላቸዋለች፡፡ ሌሎች በጦሩ ያለፉ መኮንኖች ካንቺ በፊት ስለኮ/ል ካሣ በመጻሕፎቻቸው ማንሳታቸው፤ አንቺም በዚህ መጽሐፍሽ ግሩም አድርገሽ ማቅረብሽ እና እንዲሁም እርሳቸውን የሚያውቁ በሕይወት ያሉ የጦር ባልደረቦች ምንጊዜም በትካዜ ለሌሎች ማውጋታቸው እና በውስጠ ሕሊናቸው ማሰላሰላቸው፤ ማንሳታቸውና ማስታወሳቸው አይቀሬ ነውና እንደተመኙት ታሪክ መሰከረችላቸው እንጂ አልመሰከረችባቸውም፡፡

ለአገራችን ውድቀት ውጫዊና ውስጣዊ ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ በአገር ደረጃ ቅጥ ባጣና ለማንም ካለዕውቀት፤ካለልምድ እና ካለደረጃ የተምበሸበሸ የጄኔራልነት እና የሌላም ሹመት ለኮ/ል ካሣ ምናቸውም ሊሆን አይችልምና በዚህ ቅር አይበልሽ፡፡ ኮ/ል ካሣ እና ሌሎች እኩዮቻቸው ሆነ የበታቾቻቸው እና አኩሪ የውጊያ ገድል የፈጸሙ ወታደሮች ጭምር ለደረጃ ዕድገት እና ለሹመት ያለመብቃታቸው ምንም ያህል አያስቆጭም፡፡ ከስንት አንዱ ይሆን በሥራ፤በችሎታ፤በልምዱ ተመዝኖ የተሾመው? ጀግና ምንጊዜም ጀግና ነው፡፡ ራሱን ለአገሩ አንድነት በቆራጥነት ሕይወቱን የሰዋ እንኳንስ እንደኮ/ል ካሣ ያሉ የጦር መሪ ይቅርና አብሮዋቸው የተሰው ሁሉ የጀግኖች ጀግና ከአንዳንድ ከንቱ የአቋራጭ ተሿሚ ጄኔራሎች በላይ ጄኔራሎች ናቸው፡፡ ሕዝብና ታሪክ መስክረዋል፡፡ ተግባር አሳይቷል፡፡ ጀግናው በላይ ዘለቀ የተከታዮቻቸውን ሹመት ለጃንሆይ ለማጸደቅ ሲያቀርቡ፤ጃንሆይ ይሀን ሁሉ ሹመት ስትሰጥ እራስህንስ ምን ብለህ ሾምክ? ብለው ሲጠይቋቸው የበላይ ዘለቀ መልስ አጭር፤ ፈጣንና ግልጽ ነበር፡፡ እኔማ አንዴ እናቴ በላይ ብላኛለች ነበር፡፡ካሣም እንዲሁ የወላጆች ብቻ ሳይሆን የአገር ካሣ ሁነው አልፈዋል፡፡ ለዚህም ታሪክ መስክራላቸዋለች፡፡ በአንቺ ምክንያትም ታሪካቸው የበለጠ መነጋገሪያ ሁኗል፡፡ከፍተኛ የህሊና እርካታም እንዳገኘሽበት ተረድቻለሁ፡፡

መልካሙን ሁሉ እመኝልሻለሁ፡፡

ታዬ ብርሃኑ