የታሪክ አደራ፣ የኢትዮጵያዊነት ፍቅርና ጽናት፣ ወኔና መሥዋዕትነት የተስተጋባበት፡- “ታሪክ የምትመሰክርልን …”

(ከሰንደቅ ጋዜጣ ድረገጽ – ምልከታ ከሚለው አምድ ላይ የተወሰደ senedeknews.com/milketa.html)

Wednesday, 19 July 2017 13:41

/ ካሣ ገብረ ማርያም (1923-1971)

በተረፈ ወርቁ 

እንደ መንደርደሪያ፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበራቸው በተለያየ የሥራ ኃላፊነት ላይ፣ በሲቪልና በሚሊታሪ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች እያወጧቸው ያሉት መጽሐፎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸው መልካም ዜና ነው። አብዛኛው የትናንትናው ትውልድ ታሪክና ረጅም የትግል ጉዞውና መሥዋዕትነቱ በወጉ ባልተቀመረበትና በስፋት ባልቀረበበት ኹኔታ እንዲህ ዓይነቶቹ መጽሐፎች መታተም ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ አያጠራጥርም። በዚህ ረገድም የትናንትና ታሪካችን የተሟላና ሙሉ ቅርጽ የያዘ እንዲሆን ለሚደረገው ጥረት ጥሩ አበርክቶት እንደኾነ በግሌ አምናለሁ።

‹‹ታሪክ ትውልድ መሸጋገሪያ ድልድይ ነው!›እንዲሉ በተጨማሪም የዛሬው ትውልድ የትናንትናው ትውልድ፣ ጀግኖች አባቶቹና እናቶቹ ስለ አገራቸውና ወገናቸው የነበራቸውን ፍቅርና ተቆርቋሪነት፣ የከፈሉትን ግዙፍ መሥዋዕትነት፣ ያለፉባቸውን ውጣ ውረዶችና ጠመዝማዛ መንገዶች፣ ብርታታቸውንና ድካማቸውን፣ ቁጭታቸውንና ብሶታቸውን፣ ድልና ሽንፈታቸውን፣ ከብረት የጠነከረ ወኔያቸውን፣ ጀግንነታቸውንና ብርቱ ተጋድሎአቸውን፣ ርእያቸውንና ተስፋቸውን … እንደ መስታወት የሚያሳዩ በመሆናቸው የእንዲህ ዓይነቶቹ የታሪክ መጻሕፍት መውጣት መበራከት ይበል የሚያሰኝ ነው።

በዚህም መሠረት ሀገራችን ያለፈችበትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበረሰባዊ ውስብስብ የታሪክ ሂደቶችን በማስቃኘት ረገድ ፋይዳቸውና ጠቀሜታቸው ከፍ ያሉ የታሪክ መጻሕፍት በየጊዜው እየወጡ ነው። በዚህ ረገድም በቅርቡ በሒልተን ሆቴል የኮ/ል ካሣ ገ/ማርያምን የሕይወት ታሪክ የያዘ መጽሐፍ በልጃቸው በዶ/ር ስንታየሁ ካሣ ተጽፎ ለምርቃት በቅቷል።

ይኸው ማጣቃሻዎችን /References እና መጠቁሞችን/ Index ጨምሮ በ423 ገጾች የተቀነበበው መጽሐፍ የመጀመሪያው እትም በሀገረ በአሜሪካ ሎሳንጀለስ በወርኻ ኅዳር ታትሞ ለንባብ የበቃ ሲሆን ሁለተኛው ሕትመት ደግሞ በሀገራችን ኢትዮጵያ በኢንተርናሽናል ሊደር ሺፕ ኢንስቲትዩት የሕትመት ሥራ አማካኝነት በወርኻ ግንቦት የታተመ እንደሆነ መጽሐፉ ውስጥ የተካተቱ መረጃዎች ያሳያሉ። በእርግጥ ከመጽሐፉ የምረቃ ቀን ድረስ ይህ መጽሐፍ በኢትዮጵያ ገና ለሽያጭ አልቀረበም።

በዚህች አጭር ጽሑፍ በኮ/ል ካሣ ገ/ማርያም ሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ላይና በሒልተን ሆቴል በነበረው የመጽሐፉ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ከመጽሐፉ ደራሲ ከሆኑት ከዶ/ር ስንታየሁ ካሣ ጀምሮ በዝግጅቱ ላይ የታደሙ የቀድሞ የደርግ መንግሥት ከፍተኛ ባለ ሥልጣናትና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ያነሷቸውን ሐሳቦችና አስተያቶች መሠረት በማድረግ ጥቂት ነገሮችን ለማለት ወደድኹ።

  1. የዘጠኝዓመት ምጥና ውጣ ውረድ ፍሬ፡

በሙያቸው የሕክምና ባለ ሙያ የሆኑትና በሀገራችን በተለያዩ ከተማዎች ሙያዊ አገልግሎታቸውን ያበረከቱት ዶ/ር ስንታየሁ ላለፉት በርካታ ዓመታት ደግሞ ኑሮአቸውንም ሆነ ሥራቸውን በአሜሪካ አገር ያደረጉ ጠንካራ ሴት ናቸው። ዶ/ር ስንታየሁ ይህን የአባታቸውን የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ለመጻፍ ዘጠኝ ዓመታት የወሰደባቸው እንደሆነ ነው በምርቃቱ ሥነ ሥርዓት ላይ የተናገሩት። በዚህ ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ እጅግ አድካሚ በሆነው፣ ጽናትን፣ ብርቱ ትዕግሥትንና ወኔን በሚጠይቀው ሂደት የአባታቸውን የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ለመጻፍ ዶክተር ስንታየሁ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል በሚል በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያላንኳኩት በር፣ ያላገኟቸው ሰዎች የሉም ማለት ይቻላል።

በዚህ የሥራ ሂደትም ዶ/ር ስንታየሁ ኑሮአቸውን በዚምባቡዌ ካደረጉትና የሀገራችን ፕሬዝዳንት ከነበሩት ከኮ/ል ጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ጀምሮ፣ የቀድሞ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፕሬዝዳንት መ/አ ግርማ ወ/ጊዮርጊስን ጨምሮ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከመቶ የሚልቁ በርካታ ሰዎችን በአካል፣ በስልክ፣ በኢሜይልና በደብዳቤ ቃለ መጠይቅ አድርገዋል፤ እንዲሁም በዘመኑ በከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ ላይ ከነበሩ ከእነዚህ ሰዎች ጋር በዛን ዘመን በነበረችው ኢትዮጵያችን የታሪክ ጉዞ ሂደት ላይም በርካታ የሆኑ ጠቃሚ ሐሳቦችንና መረጃዎችን ተለዋውጠዋል።

ዶ/ር ስንታየሁ በሀገራችን መረጃዎችን ለማግኘት ያለውን አድካሚና እጅግ አታካች የሆነ ሂደት በድል ተወጥተውና መከላከያ ሚ/ር መስሪያ ቤት ድረስ ዘልቀው በመግባት የአባታቸውን የግል ማኅደር በመመርመር የተሟላ ሊባል በሚችል ደረጃ የአባታቸውን የኮ/ል ካሣሁን ገ/ማርያምን የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል። ዶ/ር ስንታየሁ በሙያቸው የሕክምና ሰው ቢሆኑም እንደ አንድ የታሪክ ባለ ሙያ ሰው በተቻላቸው አቅም ሁሉ አባታቸውን በተመለከተ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና እስከወሰዱበት ጊዜ ድረስ – ከአባታቸው ጋር የነበራቸውን ጥብቅ የሆነ ቤተሰባዊ ግንኙነት፣ ከቤተሰብ ከወዳጅ ዘመድና ከአባታቸው ጓደኞች ጋር ያሳለፉትን የልጅነት ጣፋጭ ጊዜያቸውን፣ በልባቸው ጽላት ለዘላለም የታተመውን የአባታቸውን፣ የሀገራቸውን ኢትዮጵያ ብርቱ ናፍቆትና ትዝታ ቀለል ባለና ለዛ ባለው ቋንቋ በመጽሐፋቸው ውስጥ በሚገባ ተርከውልናል።

በታሪክ አጻጸፍ ሥነ ዘዴ /Methodology ሁለተኛ የታሪክ መረጃዎችን /Secondary Sources መሠረት አድርጎ ለመጻፍ ብዙ ልፋትና ድካም ያለው ሲሆን ከፍተኛ ጥንቃቄም የሚያሻው ነው። የዶ/ር ስንታየሁን በመረጃና በማጣቀሻዎች የታጨቀ መጽሐፍ ላገላበጠ ዶክተሩ የአባታቸውን ታሪክ እውነተኛና ሚዛናዊ ለማድረግ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል ማለት የሚቻል ይመስለኛል። የ፳ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ዕውቅ ሀገራችን ምሁር የነበሩት ‹ፖለቲካል ኢኮኖሚስቱ› ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ የሀገራችንን ታሪክና የኢኮኖሚ ሁኔታ በተነተኑበት ድንቅ መጽሐፋቸው፡- ‹‹ታሪክ ለመጻፍ ከወገንተኝነት የጸዳ፣ ስሜታዊነት እንደፈለገ የማይነዳው፣ እውነተኝነትን/ሐቅን መሠረት ያደረገ፣ ሙያዊ ሥነምግባርና ፍሪሃ እግዚአብሔር የተላበሰ ማንነት፤›› በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል።

በዚህ ረገድ የኮ/ል ካሣ ገ/ማርያም የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ጸሐፊ የሆኑት ዶ/ር ስንታየሁ በአካዳሚያው ዓለምና እንዲሁም ለረጅም ዓመታት በቆዩበት የሕክምና ሙያ የጥናትና ምርምር ሥራቸው ባካበቱት ከፍተኛ የሆነ ሙያዊ ሥነ ምግባርና ብቃት መጽሐፋቸውን ሚዛናዊ፣ በበቂና በበርካታ መረጃዎች የተደገፈ ለማድረግ ያደረጉትን ጥረት በሚገባ አግዞታል ለማለት እደፍራለሁ። ጸሐፊዋ መጽሐፋቸውን በእውነተኛ/በሐቀኛ በሆኑ መረጃዎች ላይ የተደገፈ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የዘጠኝ ዓመታት ብርቱ ምጥ፣ ጥረትንና ትዕግሥትን ጠይቋቸዋል። በምስል፣ በድምፅ፣ በድምፅ ወምስል የሚገኙ መረጃዎችን፣ ታሪካዊ ፋይዳቸው ከፍ ያሉ በርካታ ወታደራዊ፣ ምሥጢራዊ ሰነዶችንና መዛግብትን በመፈተሽ፣ የአባታቸውን የግል ማኅደር በመመርመር የአባታቸውን ታሪክ የተሟላ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ ጥረትን አድርገዋል። ዶ/ር ስንታየሁ ለዚህ ጥረታቸውና ልፋታቸው በዕለቱ ከፍተኛ ክብርና ምስጋና ተችሯቸዋል።

  1. የአንድእናት ልጆችን በናፍቆት ስስት፣ በቁጭት እንባ ያራጨ ገጠመኝ፡

በግሌ እጅጉን ያስገረመኝና ዶ/ር ስንታየሁ በሒልተን ሆቴል በመጽሐፉ የምረቃ ዕለት ባደረጉት ንግግራቸው ብርቱ የናፍቆትና የትዝታ ስሜት በተጫነው ድምፀት የተረኩትንና በመጽሐፋቸው ውስጥም ያካተቱትን አሳዛኝም የሚያስቆጭም የሆነ አንድ ገጠመኛቸውን እዚህ ላይ ለማንሳት እወዳለኹ። ዶ/ር ስንታየሁ የአባታቸውን የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ለማሰናዳት በደከሙባቸው ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ከአባታቸው ከኮ/ል ካሣሁን/ከደርግ ሠራዊት በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው ሲፋለሙ ከነበሩ የቀድሞ የሻቢያ/የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር ሰዎች ጋር ሳይቀር ለመገናኘት ዕድሉን አግኝተው ነበር።

ታዲያ በአንድ ወቅት ለዚሁ መጽሐፋቸው መረጃዎችን ሲያሰባስቡ በጠቋሚ ሰዎች አማካኝነት በትጥቅ ትግሉ ዘመን የሻቢያ ሠራዊትን በሕክምና ሙያ ስታገለግል ከነበረች ነርስና ኑሮዋን በሀገረ አሜሪካ ካደረገች ሴት ጋር ይገናኛሉ። ዶ/ር ስንታየሁ ከዚህች የቀድሞ የሻቢያ ታጋይ ጋር በነበራቸው ቆይታም በኤርትራ ክፍለ ሀገር በተደረገው ጦርነት ወቅት፣ ከጦሩ አዛዥ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት የተነሣ ‹በሮራ ፀሊም› የጦር ግንባር የገዛ ሽጉጣቸውን ጠጥተው ስለሞቱት ስለ አባታቸው ስለ ኮ/ል ካሣሁን ገ/ማርያም አንድ የታሪክ መጽሐፍ እየጻፉ እንደሆነና ስለ አባታቸውና በዘመኑ በደርግና በሻዕቢያ ሠራዊት መካከል ስለነበረው የእርስ በርስ ጦርነት የምታውቀውን መረጃ እንዲሰጧት ጥያቄያቸውን ያቀርቡላታል።

ቀድሞ የሻዕቢያ ሠራዊት የሕክምና ባለሙያና ታንከኛ ታጋይ ሴት የዶ/ር ስንታየሁን ንግግር እያዳመጠች ያን አስከፊ ጦርነት፣ የእርስ በርስ እልቂት ትእይንት በትዝታ ወደ ኋላ ተጉዛ እያሰታወሰች በእንባ ትታጠብ ጀመረ። ይህች ሴት በእንባና ሳግ ውስጥ ሆናም ለዶ/ር ስንታየሁ እንዲህ አለቻቸው።

‹‹… የሚገርምሽ እኔ በሻዕቢያ ሠራዊት ጎን ተሰልፌ ለኤርትራ ነጻነት ስፋለም ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን የነበረው ወላጅ አባቴ ደግሞ በናቅፋ ግንባር ተራሮች ሕይወታቸው ከተሠዉ የደርግ ኮሎኔሎች መካከል አንዱ ነበር። በዛ ደም እንደ ጎርፍ በጎረፈበት፣ የሰው ልጅ ክቡር አካል በካባድ መሳሪያ እየተመታ እንደ ዶሮ ብልት በተገነጣጠለበትና እየተበጣጠሰ የትም በወደቀበት፣ የአንድ እናት ምድር ልጆች፣ የአንድ ማኅፀን አብራክ ክፋይ ልጆችአባትና ልጅ፣ ወንድምና ወንድም፣ እህትና እህት በተቃራኒ ጎራ ተሠልፈው የኤርትራ ምድርየናቅፋ ተራሮች በደም አበላ በታጠቡበት፣ ምድሪቱ ገሃነም፣ የደም ምድር-‹አኬልዳማበሆነችበት በአሳዛኙ በናቅፋ ግንባር ነው ውድ አባቴን ያጣሁትባይገርምሽ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ታንክ እየነዳሁ አዲስ አበባ ከገባሁት የሻዕቢያ ታጋዮች መካከል እኔ አንዷ ነበርኩ

ከዚህ በኋላ አባቶቻቸውን በኤርትራ ተራሮች በመሥዋዕትነት ለዘላለም ያጧቸው በዶ/ር ስንታየሁና በዚህች የቀድሞ ሻዕቢያ ታጋይ በነበረች ሴት መካከል ንግግር ሳይሆን ቁጭትና ናፍቆት፣ ሰቀቀንና ትዝታ እንደ እሳት እየፈጃቸው በጉንጮቻቸው ላይ የሚወርደው እንባ ነበር ቋንቋቸው፣ መግባቢያቸው የሆነው። ሁለቱ የአንድ አፈር፣ የአንድ እናት ልጆች የአባቶቻቸውን አሳዛኝ ሕልፈት ወደ ኋላ ተጉዘው እያሰቡ በእንባ መታጠብ ጀመሩ። ዶ/ር ስንታየሁ ይህን ገጠመኛቸውን ሲተርኩ በሒልተን ሆቴል አዳራሽ በመጽሐፍ ምረቃ ውስጥ ታድመን የነበርን የቀድሞ የደርግ መንግሥት ከፍተኛ ወታደራዊ ሹማምንትና በርካታ እንግዶች በኀዝን፣ በቁጭት ድባብ ውስጥ ነበር የከተተን።

  1. የአንድነት፣ የዕርቅና የሰላም ያለህ ናፍቆትና ሰቀቀን የታከለበት ጩኸት፡

ዶ/ር ስንታየሁ የአባታቸውን የኮ/ል ካሣ ገ/ማርያም የሕይወት ታሪክ መጽሐፋቸው ውስጥ ለሀገራቸው ኢትዮጵያና ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነትና አብሮነት ያላቸውን በጎ ምኞትና መልካም ርእይ ለመግለጽ የሞከሩበትንና በንኡስ ርእስነት በአጭሩ ለማየት የሚሞክረውን አስተያየቴን በአፍሪካዊው ጀግና በኔልሰን ማንዴላ ዕውቅ ንግግር መግቢያነት ለመጀመር ወደድኹ። እንዲህ ይነበባል፤ “The path of those who preach love, and not hatred, is not easy. They often have to wear a crown of thorns.” ~Nelson Mandela from a Message to the Global Convention on Peace and Non-violence, New Delhi, India, 31 January 2004.

የኮ/ል ካሣ ገ/ማርያም የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ጸሐፊ ዶ/ር ስንታየሁ የጠላትነት፣ ቂም በቀል ቁርሾ ታሪክ ለማናችንም አይጠቅመንም፤ ይልቅስ ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለአንድነት እጅ ለእጅ እንያያዝ የሚለውን ተማሕጽኖን፣ ልመናን ያስቀደም የሚመስል ብርቱ ቁጭት የታከለበት ገጠመኛቸውን በመጽሐፋቸው ውስጥ በተለያዩ ስፍራዎች ውስጥ ለማካተት ሞክረዋል።

ይህን የዶ/ር ስንታየሁን የሰላም፣ የአንድነትና የዕርቅ ያለህ የተማጽኖ ድምፃቸውን፣ ጩኸታቸውን ለማንሳት የተገደድኩበት ምክንያት ሰላም የሰው ልጆች ሁሉ አንገብጋቢ ጥያቄ በመሆኑና በመጽሐፉ ምረቃ ዕለት በነበረው የአስተያየት፣ ጥያቄና መልስ ወቅት አንድ የቀድሞ የደርግ መንግሥት ከፍተኛ ባለ ሥልጣን የነበሩ ሰው በአንድ የጦር መሪ ላይ ያነሡት የወቀሳ ሐሳብ ነው።

እኚሁ የቀድሞ የደርግ መንግሥት ከፍተኛ ባለ ሥልጣን የአንድ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን አዛዥ ስምን ለይተው በመጥቀስ በኤርትራ በሮራ ፀሊም ግዳጅ ላይ ለነበረው ሠራዊትና ለኮ/ል ካሣሁን ህልፈት ተጠያቂው እኚህ ሰው ናቸው በማለት በምሬትና በቁጭት ስሜት ያነሡት ሐሳብ እስካሁንም ድረስ የዛ ትውልድ አባላቶች የሆኑ አንዳንድ ሰዎች እንደ ደቡብ አፍሪካዊው ኔልሰን ማንዴላ፣ እንደ አፍሪካ አሜሪካዊው የጥቁሮች መብት ታጋይ ዶ/ር ማርቲን ሉተር፣ እንደ ህንዳዊው የነጻነት አባት ማኅተመ ጋንዲ ሰላምን፣ ይቅርታንና ዕቅርን የሚሰብክ ቅን ልቦንና፣ በጎ ሕሊናን ያልታደሉ መሆናቸውን ያሳየ ነው።

አስገራሚው ነገር የእኚህ ቀድሞ የደርግ ባለ ሥልጣን ወቀሳ ከአዳራሹ ወጥተን የሻይ ቡና ሥነ ሥርዓት ላይ በነበርንበት ጊዜ ከአንድ ሌላ ከፍተኛ ደርግ መኮንን ከሆኑ ብርጋዴር ጄኔራል ጋር ኃይል ቃል የታከለበት መከራከሪያ አርእስተ ጉዳይ ሆኖ ነበር። ብርጋዴር ጄኔራሉ ዕጣ ፈንታና መሥዋዕትነት በሚል ርእስ በጻፉት መጽሐፋቸው ውስጥ በወቀሳ ስለተነሡት ወታደራዊ አዛዥ ምስክርነት የሰጡበት አንቀጽ፤ ‹የአንድ አካባቢ ተወላጅ ስለሆናችሁ ነው፣ ስለ እርሱ የጻፍከው፤› በሚል ትርጓሜ በዘመናችን የተንሰራፋው የዘረኝነት/የጎሰኝነት ልዩነትና ጥላቻ – እነርሱና እኛ በሚል የትናንትና ታሪካችንን የቂም በቀልና የጥላቻ ጃኖ አልብሶ ወዴት እየወሰደን እንደሆነ የታዘብኩበት አሳዛኝ ገጠመኜ ነው።

በዕለቱ ካጋጠመኝ ከዚህ ትዝብቴ ስመለስም ዶ/ር ስንታየሁ የአባታቸውን ታሪክ መጽሐፍ ለመጻፍ መረጃዎችን ለመሰብሰብ በተጓዙበት ወቅት ያጋጠሟቸውን ሰዎች፣ የነገሯቸውን አስደናቂ ታሪኮችና ገጠመኞች የተረኩበት ምዕራፍ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝቦች መካከል- እንዲሁም በአፍሪካና በመላው ዓለም ያሉ ሕዝቦች በሰላም፣ በፍቅርና በወንድማማችነት መንፈስ ተከባበሮ መኖር ያላቸውን በጎ ምኞታቸውንና ጥልቅ ፍላጎታቸውን ያሳዩበት ነው ማለት ይቻላል።

ከዚሁ በጎ ምኞታቸው ጋር ተያይዞም በአንድ ወቅት ዶ/ር ስንታየሁ በሀገራችን ባለ የጦር አካዳሚ የተመረቁና በኋላ ግን የሻዕቢያ ሠራዊት አባል የሆኑ መኮንን አግኝተው ያደረጉትን ጭውውት እንዲህ ተርከውታል። ሁለት ኤርትራ የተወለዱ አብሮ አደጎች አንዱ ከደርግ ሌላኛው ከሻዕቢያ ሠራዊት ጋር ተሠልፈዋል። እናም አንደኛው በትውልድ ከተማው ሆኖ በሠርግ ሲያገባ ሌላኛው በጦር ሜዳ የነበረው ጓደኛው ወሬው ይደርሰዋል። ‹‹እንዴት አብሮ አደግ ጓደኛዬ ሠርግ ደግሶ ሲያገባ አልጠራኝም!›› ብሎ ይናደዳል። ጓደኞቹም፤ ‹‹እንዴ ጤነኛ አይደለህም እንዴ?! እንዴት አድርጎ ነው ሊጠራህ የሚችለው? እንደው ቢጠራህስ እንዴት አድርገህ ነው በጠላት ወረዳ ውስጥ የሠርጉ ታዳሚ የምትሆነው?! በማለት ይጠይቁታል። ይህ ወታደርም በወታደራዊ ግዳጅ ላይ ለነበሩት ጓዶቹ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፡- ‹‹ቀላል ነው ለሠርጉ ቀን የሰላም ነጭ መሀረብ እያውለበለብኩ መግባት እችል ነበር።

ዶ/ር ስንታየሁ እነዚህንና ሌላ ተመሳሳይ ገጠመኞቻቸውን በማንሳት ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ያላቸውን በጎ የሰላም ምኞት፣ የአንድነት፣ የሰላምና የዕርቅ ያለህ ድምፃቸውን፣ ጩኸታቸውን የጀግና አባታቸውን የኮ/ል ካሣ ገ/ማርያምን የሕይወት ታሪክ በጻፉበት መጽሐፍ ከፍ አድርገው አሰምተዋል። ዶ/ር ስንታየሁ በዚሁ መጽሐፋቸው ውስጥ ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ አህጉራችን አፍሪካና መላውን ዓለም በፍቅር፣ በይቅርታ ገመድ የሚያስተሳስሩ ሰላምንና ዕርቅን የሚሰብኩ ማንዴላዎች እንደሚያስፈልጉን በምሳሌዎች ጭምር አስደግፈው በቁጭት ለማንሳት ሞክረዋል።

  1. / ካሣ /ማርያም ማንነት በጨረፍታ፡

ኮ/ል ካሣ ገ/ማርያም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ሥልጠናን የወሰዱ፣ በሚሊታሪ ሳይንስ ዕውቀት የበሰሉ፣ ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ዲስፕሊን የተላበሱ መኮንን መሆናቸውን በዕለቱ በመጽሐፉ ምረቃ ላይ ከነበሩት የሥራ ባልደረቦቻቸውና ከሚያውቋቸው ሰዎች ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ተሰምተዋል። እንደ እነ ሜ/ር ጄኔራል ካሣዬ ጨመዳ፣ እንደ እነ ብርጋዴር ጄኔራል ዋሲሁን ንጋቱና ኮ/ል ፍስሐ ደስታ ያሉ የቀድሞ ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት፣ የጦር መኮንኖችና አዛዦች የቁጭት ስሜት የተቀላቀለበት አስተያየታቸው የዛሬው ትውልድ ከእነዚህ ባለ ታሪኮች ከጥንካሬያቸው፣ ከጽናታቸው፣ ከብረት ከጠነከረ ወኔያቸው፣ ከትዕግሥታቸው፣ ከሥሕተታቸውና ከድካማቸው መማር የሚችልበት ዕድል አሁንም ገና እንደሆነ ያሳየ ነበር።

ዶ/ር ስንታየሁ በመጽሐፋቸው ውስጥ ከቀድሞ የኢሕዲሪ ፕሬዝዳንት ከኮ/ል ጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ጀምሮ እስከ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ከነበሩት መ/አ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ በርካታ የደርግ መንግሥት ከፍተኛ ሹማምንትና ባለሥልጣናት በወቅቱ የአብዮት ዋዜማ፣ መባቻና ማግሥት ሂደት ውስጥ ስለነበረችው ሀገራችን ኢትዮጵያና ስለ ኮ/ል ካሣ ገ/ማርያም የሚያውቁትን፣ ያዩትና የሰሙትን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ለአብነት ለመጥቀስ ያህልም በመጽሐፉ ምረቃ ዕለት በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩትና ለዚሁ መጽሐፍ ምረቃ ሲሉ ከሀገረ ካናዳ የመጡት ኮ/ል ስምረት መድኀኔ፤ ኮ/ል ካሣ ገ/ማርያም በሀገራችን የበረራ ድኅንነት/አንቲ ሃይጃክ ሥልጠናን በዋና መሪነት በማቋቋምና የሥራ ባልደረቦቻቸውን በማስተባበር በተለያዩ ጊዜያት በሀገር ውስጥ በውጭ ሀገር የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጠለፋ ሙከራዎችን ያከሸፉባቸውን አስገራሚ የሆኑ ኦፕሬሽኖችን አስታውሰዋል።

በሀገር ውስጥ፣ በካርቱም፣ በፍራንክ ፈርት፣ በየመን፣ በካራቺ፣ በሮም፣ በስፔን፣ ማድሪድ፣ በሊቢያ፣ ቤንጋዚና በግብጽ፣ ካይሮ የበረራ ደኅንነት ሆነው በከፍተኛ ብቃት የተወጧቸውን ኃላፊነቶችና የመሯቸውን ውጤታማ ኦፕሬሽኖች ዶ/ር ስንታየሁ በመጽሐፋቸው ውስጥ በሚገባ ጠቅሰውታል። ኮ/ል ካሣ በሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት፣ በሐረር የጦር አካዳሚ፣ በውጭ ሀገር በአሜሪካ፣ በዩጎዝላቪያ ከፍተኛ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን በሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት በአዛዥነት፣ በሐረር የጦር አካዳሚ ደግሞ በአስተማሪነት፣ በበረራ ድኅንነት ሙያና በተለያዩ ወታደራዊ ግዳጆች ሀገራቸውን አገልግለዋል።

ኮ/ል ካሣ ገ/ማርያም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በተለያዩ ሥራ ኃላፊነቶችና ግዳጆች ለሀገራቸው ኢትዮጵያ ታላቅ የሆነ መሥዋዕትነትን ከፍለዋል። እኚህ ጀግና በመጨረሻም በሰሜን ግንባር ጦርነቶች በወታደራዊ ግዳጅ ላይ እያሉ በኤርትራ ሮራ ፀሊም በ1971 ዓ/ም የገዛ ሽጉጣቸውን ጠጥተው የተሠዉ ኢትዮጵያዊ ጀግና መኮንን ናቸው። እስከ ዛሬ ድረስ እምብዛም ያልተነገረላቸውን የእኚህን ጀግና ታሪክ ሙሉ ገጽታ ለማግኘት በልጃቸው በዶ/ር ስንታየሁ ካሣ የተጻፈውን ‹‹ታሪክ የምትመሰክርልን…›› ካሣ ገብረ ማርያም 1923-1971 የሚለውን መጽሐፍ ማንበብ አስፈላጊ ነው።

በመጨረሻም ዶ/ር ስንታየሁና የዚህ መጽሐፍ ምረቃ አዘጋጅ ኮሚቴ በዚህ ታላቅ ታሪካዊ ዝግጅት ላይ በሀገራችን የሚገኙ ከኤሌክትሮኒስም ሆነ ከሕትመት መገናኛ ብዙኃኖች/ሚዲያዎች ሽፋን እንዲሰጡ ምንም ባለሙያ አለመጋበዛቸው ዝግጅታቸውን በከፊል ቢሆን ጎዶሎ አድርጎታል ማለት የሚቻል ይመስለኛል። ይህን የበርካታ የቀድሞ የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ሹማምንቶች ጥሪ ተደረገላቸው እንግዶች የተገኙበትንና ደስ የሚሉ ጠቃሚ ሐሳቦችና አስተያየቶች በተንሸራሸሩበት መድረክ፣ የብዙዎች የታሪክ ምስክርነት፣ የቀደሙት ትውልዶች ለሀገራቸው ኢትዮጵያና ለአሁኑ ትውልድ ያላቸውን መልካም ርእይና በጎ ምኞት የገለጹበትን ይህን ታሪካዊ ክስተት በሒልተን ሆቴል ጣር ስር ለጥቂትና ለተመረጡ እንግዶች ብቻ መገደብ፣ መወሰን በእውነቱ የሚገባ አልነበረም።

በኮ/ል ካሣ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍና የምረቃ ዝግጅት ላይ ያደረግሁትን አጭር ዳሰሳ በኮ/ል ካሣ ገ/ማርያም ምርጥ አባባል ለመቋጨት እወዳለኹ። ታሪክ እኛንም በሕሊና መነጽሯ እየተመለከተች ነው፤ የምትመሰክርልን እንጂ የማትመሰክርብን እንዲሆን እመኛለሁ። አበቃሁ!

ሰላም!