ጀግናው ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያምን ለማስታወስ በቨርጂኒያ የተደረገ ልዩ ዝግጅት

በአዘጋጅ ኮሚቴው

እአአ በማርች 18 ቀን 2017 ዓ/ም ቨርጂንያ በሚገኘው የመዓዛ ሬስቶራንት ጀግናው ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያምን ለመዘከርና በልጃቸው በዶ/ር ስንታየሁ ካሣ የተጻፈውን የሕይወት ታሪካቸውን የሚገልጸው መጽሐፍ ለመመረቅ ቁጥሩ ከሦስት መቶ በላይ ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሰው ተገኝቷል። ከዚያም ውስጥ በርካታ የቀድሞው ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፥ ሚኒስትሮች፥ አምባሳድሮችና ሌሎችም የተከበሩ እንግዶች ነበሩበት።

ሲጀመር ሦስት የደምብ ልብስ የለበሱ የቀድሞ ሠራዊት አባሎች የኢትዮጵያ እና የአሜርካ ሰንደቅ ዓለማዎችን ይዘው በመቅደም የኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም ቤተሰቦችን አስከትለው ሲገቡ እንግዶቹ በደመቀ ጭብጨባ ተቀበሏቸው። ከዚያም በቀይ ጨርቅ የተሸፈነውን የመጽሐፉን ሽፋን የሚያሳየውን ትልቅ ፓስተር ሦስት የኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም የልጅ ልጆች በመግለጥ መጽሐፉን ይፋ አደረጉት። አንዱ የልጅ ልጃቸው፥ ካሣ ካሣሁን፥ በአያቱ ስም በመጠራቱ ኩራትና ክብር እንደሚሰማውና ብዙ ሰዎች መጽሐፉን እንደሚያነቡት ተስፋ ማድረጉን ገልጸና እናቱን በማስተዋወቀ መድረኩን ለቀቀ። እናቱ፥ ዶ/ር ስንታየሁ ካሣ፥ መጽሐፉን እንዴት ለማዘጋጀት እንደበቃች፥ አባቷ ምን ያህል ቤተሰባቸውን ይወዱ እንደነበር፥ ተጫዋች አዝናኚና መልካም ሰው እንደነበሩ በአጭሩ ገልጻ፥ ዝግጅቱን ያስተባበሩትን የኮሚቴ አባላትና በዝግጅቱ ለመሳተፍ የመጡትን እንግዶች በማመስገን ንግግሯን አጠቃለለች።

ቀጥሎ የቀረቡት ብ/ጄኔራል ውበቱ ፀጋዬ ሲሆኑ፥ እሳቸውም ከአስራ አምስት ዓመት በላይ በኤርትራ ያገለገሉና ስለ ሰሜኑ ጦርነት መጽሐፍ የጻፉ መሆናቸው ይታወቃል። በንግግራቸውም በቅርበት ያዩትንና የተገነዘቡትን የኮሎኔል ካሣ ገብረማርያምን የጦር ሜዳ ጀብዱ በዝርዝር ሲገልጹ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከነበሩት እውቅ የጦር ሜዳ መሪ ጄኔራሎች ሥራ ጋር በማዛመድ አቅርበውታል። በመጀመሪያው ምዕራፍ የግብረ ኃይል ዘመቻና በናቅፋው ግንባር የነበረውን የኮሎኔል ካሣን የመጨረሻ ግዳጅ አመራርን በማድነቅ የዓይን ምሥክርነት ሰጥተዋል።

ሻለቃ ንጋቱ ቦጋለም እንደዚሁ ስለ ጦርነቱ መጽሐፍ የጻፉ ሲሆን፥ በዚህ ዝግጅት የቀረቡት የሐረር ጦር አካዳሚ 21ኛ ኮርስ ምርቆችን ወክለው ነበር። በሱማሊያ ወረራ ምክንያት የ21ኛው ኮርስ ሆለታ ሲሰለጥን አዛዡ ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም ነበሩ። መንግሥት እኚህን ለጋ ወጣቶች ወደ ጦር ሜዳ ሊልክ ሲወስን ኮሎኔል ካሣ ከእግረኛ ይልቅ በተለያዩ ኪነታዊ ክፍሎች ተመድበው ቢሰለጥኑ ይበልጥ ይጠቅማሉ በማለት የበላይን አሳምነው ሕይወታቸውን እንዳተረፉ ገልጸው፤ በሶቭየት ኅብረት መድፎች፥ ታንኮችና ራዳሮች ሥራ ሠልጥነው በሁሉም ግንባር አኩሪ ውጤት ማስመዝገብ እንደቻሉና በዚህ አጋጣሚ በዚሁ አዳራሽ የሚገኙ የኮ/ል ካሣ ልጆች የሆኑ የ21ኛ ኮርስ አባላት ለአለቃቸውና ለአስተማሪያቸው ያላቸውን ፍቅርና አድናቆት ለመግለጽ መሰባሰባቸውን ገልጸው፤ አባላቱ እንዲነሱና ታዳሚው እንዲያያቸው አድርገዋል።

ሻለቃ መስፍን ዘለቀ የዚሁ የ21ኛ ኮርስ አባል ሲሆኑ ኮ/ል ካሣ ገብረማርያም በተሰውበት በመጨረሻው ግዳጅ ላይ የተሳተፉና ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ የሆነውን ተመልክተው የተረፉ የዓይን ምሥክር ናቸው። ዝርዝሩን ሁኔታ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው እየተነተኑ አቀረቡ። ተርፈው ይህን ለመመስከር በመብቃታቸው መደሰታቸውን ሲገልጹ እንባ ሲተናነቃቸው ከተመልካቹም መሃል በመነካት ያነቡ ነበሩበት። ከዚያም በማስከተል ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር ለወቅቱ የጻፉትን ግጥም ለሕዝቡ አንበዋል፥ ሻለቃ ክፍሌ ለብዙ ዘፋኞች ግጥም በመስጠት የታወቁ ናቸው።

ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ለዚህ ዝግጅት ሲሉ ከናሚቢያ የላኩት የጽሁፍ መልዕክትም በአቶ አያልነህ እጅጉ ተነበበ። ሻለቃ ዳዊት ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያምን ያልተዘመረላቸው ጀግና ይሉና የእኝህን ጀግና ታሪክ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አስተዋውቆ በምሳሌነታቸው፥ በአርበኝነታቸው፥ በደፋርነታቸውን በውትድርና ሙያ ዕውቀታቸው ኢትዮጵያውያን እንዲኮሩባቸው፥ እንዲያከብሩአውና እንዲያስታውሷቸው ይህን መጽሐፍ በእሳቸው አምሳል የተወለደችው ልጃቸው ዶ/ር ስንታየሁ ካሣ አጠናቅቃ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማቅረቧ እጅግ እንዳስደሰታቸው ገልጸው ለፀሐፊዋም ከፍተኛ ምስጋና ያቃርባሉ። እስካሁንም ድረስ በቅርብ የሚያቋቸው ሁሉ የኮ/ል ካሣ ስም ሲነሳ ስሜታቸውን እንደሚነዝራቸው ማስተዋላቸውንና ጀግንነት፥ አርበኝነት፥ ጨዋነትና ደፋርነት ሲተረጎሙ ከኮ/ል ካሣ ምንነት ጋር በአንድነት መተያየታቸውንም ይገልጻሉ። ኮ/ል ካሣ በሠራዊቱ የተከበሩ፥ የተደነቁ፥ በጓደኞቻቸው የተወደዱ፥ በሠሩባቸው ሥፍራዎች ሁሉ የሕዝቡን ደህንነት የሚያስቀድሙ፤ ኢትዮጵያዊነትን ሕይወታቸውና ሃይማኖታቸው አድርገው የተቀበሉ፤ ብዙዎቻችንን በታላቅ ዕውቀትና ሥነ ሥርዓት ያስተማሩ፥ ብዙ ዕድሜአቸውን በግዳጅ ያሳለፉ፥ የሁላችንም አባት፥ የሁላችን ወንድም የነበሩ ታላቅ ጀግና ናቸው፤ በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል። ሻለቃ ዳዊት በእርዳታ ማስተባበሪያ ስራቸውና በጻፏቸው መጻሕፍት ይታወቃሉ።

ቀጥሎ የቀረበው የብ/ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተማርያም የቪድዮ መልዕክት ከኢትዮጵያ ነበር። ኮ/ል ካሣ ገብረማርያም የነበራቸውን የላቀ የአገርና የወገን ፍቅር፥ የወታደራዊ ሳይንስ ዕውቀትና የአመራር ብቃት በመዘርዘር ከገለጹ ወዲያ በልዩ ኃይልና የበረራ ደህንነት በእሳቸው አመራር መሥራታቸውንና ለረዥም ጊዜ እንደሚያውቋቸውም ገልጸዋል። ኮ/ል ካሣ ሁሌ እንደሚያስተምሩት ሁሉ እሳቸውም ለጠላት ጀርባችውን ላለመስጠት ቃለ መሃላ የገቡ መሆኑን እንደሚያውቁ እና  በመጨረሻም ቃላቸውን ሳያጥፉ ለአገራቸውና ወገናቸው ውዱን ሕይወታቸውን መስዋዕት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ኮ/ል ካሣ ገብረማርያም ያልተዘመረላቸው ጀግና ናቸው ታሪካቸውም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል በማለት ያበቃሉ።

ከዚህም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት  ኮሎኔል ሥምረት መድሃንዬ ከኢትዮጵያ የተላከ የቪድዮ መልዕክት ቀረበ። ኮ/ል ሥምረት የበረራ ደህንነት ሲቋቋም ም/ሥራአስኪያጅ እንደነበሩና እንዴት እንደተቋቋመ በማብራራት ጀመሩ። ከዚያም የኮ/ል ካሣና ቡድኑ ለዓለም አቀፍ የሲቪል አቭየሽን በበረራ ደህንነት ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛነት ዘክረው፤ ቡድኑ ከአውሮፓና ከአሜሪካ አይነት ከበለጸጉ አገሮች የመጣ ቢሆን ኖሮ ሥራው ምን ያህል ደምቆና ጎልቶ ይነገርለትና በታሪክም ይታወስ እንደነበር ገልጸው፤ እንዲያውም ሥራቸው ታላቅ ሲኒማ (ብሎክ ባስተር) ተሠርቶለት እነሱም ኮኮቦች ይሆኑ ነበር በማለት ደምድመዋል።

ቀጥሎም ከአትላንታ፥ ጆርጂያ የተላከው የሜ/ጄኔራል ጥላሁን አርጋው የቪድዮ መልዕክት ቀርቧል። ሜ/ጄኔራል ጥላሁን አርጋው በአሜሪካን አገር ለሁለት ዓመት በተለያዩ ክፍለ ግዛቶች በመዘዋወር የተለያዩ ወታደራዊ ትምህርቶችን አብረው በወሰዱበት ወቅት ኮሌኔል ካሣን በደንብ እንዳወቋቸውና ከዚያ መልስም እንዴት የበረራ ደህንነት እንዲያቋቁሙ እንደተመረጡ ገልጸዋል። የኮሎኔል ካሣን ባህርይ፥ የማህበራዊና ወታደራዊ ሕይወታቸውንም በቅርበት የሚያቁትን በመተንተን አቅርበዋል። የቤተሰብና የወገን ፍቅራቸውን፥ የላቀ የአመራር ችሎታቸውንና በአጠቃላይም ርህሩህ፥ ደግና መልካም አሳቢ ስለነበሩ የሚወዷቸው፥ የሚያከብሯቸውና የሚያደቋቸው መሆኑንና ልጃቸው ዶ/ር ስንታየሁ ካሣም ታሪካቸውን ለዚህ በማብቃቷ አመስግነው ለዚሁ ሲሉ ያዘጋጁትን አጭር ግጥም አንበዋል። በሕመም ምክንያት በቦታው መገኘት አለመቻላቸውን በመግለጽ በምስጋና መልዕክታቸውን አብቅተዋል።

በመጨረሻም ላይ የተለያዩ ሽልማቶች ለጸሐፊዋ ከተለያዩ ክፍሎች ተበርክተዋል። በጊዜ እጥረት ምክንያት የብ/ጄኔራል ካሣዬ ጨመዳ ከኢትዮጵያ የተላከ የጽሁፍ መልዕክትና ከእንግሊዝ አገር የተላከ የሜ/ጄኔራል መስፍን ገብረቃል የጽሁፍ መልዕክት መነበብ አለመቻሉን በትህትና ለሕዝቡ ከተገለጸ ወዲያ ዝግጅቱ ሲገባደድ፤ ፀሐፊዋ ዶ/ር ስንታየሁ ካሣ ግን መጽሐፍ የመፈረሙን ስርዓት እስከመጨረሻው ቀጥላለች።

ለዚህ ዝግጅት የመጣው ሰው ብዛት  ከተጠበቀው በላይ ለመሆኑ በመቀመጫና አዳራሽ ጥበት ሳቢያ ብዙ ሰው መመለሱ ያረጋግጣል። በዋሺንግተን ዲ ሲ አካባቢ እንደዚህ ዓይነት በርካታ ሰው ወጥቶ መጽሐፍ የመረቀበት ወቅት አለመኖሩንም ብዙ ሰዎች ገልጸዋል። ይህም የጀግናው የኮሎኔል ካሣ ገብረማርያምን ተወዳጅነት በግልጽ ያረጋግጣል። ዝግጅቱ እንዲህ የተሳካ ሆኖ እንዲፈጸም ለተባበሩን ግለሰቦች ሆነ ድርጅቶች ሁሉ ከልብ የመነጨ ምስጋናችንን እናቀርባለን።

የዝግጅቱ አቀነባባሪ ኮሚቴ።