40ኛ ዓመት መታሰቢያ

ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም የኢትዮጵያን ዳር ድንበር፥ ልዓላዊነትና አንድነት ለማስከበር ከዘውዱ አገዛዝ ጀምሮ ብዙ ግዳጆችንና ጦርነቶችን መርተው ለድል ማብቃታቸው ይታወቃል። በመጨረሻም በሰሜን፣ በሮራ ፀሊም ግዳጅ ላይ፣ ራሳቸውን በራሳቸው መስዋዕት አድርገዋል። የዚህን ዕለት 40ኛው ዓመት የመታሰቢያ በዓል ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2011 ዓ/ም በጦር ኃይሎች መኮንኖች ክበብ፣ አዲስ አበባ፣ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።

በዚህ የመታሰቢያ በዓል ላይ ጥሪ የተደረገላቸው ብዙ የቀድሞው ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖችና አባሎች፣ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩ ሲቪሎች፣ ቤተስብ፣ ወዳጅ ዘመድና አድናቂዎቻቸው ተገኝተዋል። ከአዲስ አበባ ውጭ ከአዋሳ፥ ከደብረማርቆስ፥ ከባህር ዳር እና ከመሳሰሉት ከተሞች ለዚሁ የመታሰቢያ በዓል ሲሉ የመጡ ሰዎችም ይገኙበታል። በግምትም ወደ 250 ያህል ሰው ተገኝቷል።

ኮሎኔል ካሣ የሜዳ ቴኒስ መጫወት ይወዱ ስለነበር ያንን ለማስታወስ የዕለቱ የመጀመሪያው ፕሮግራም በመሆን የሜዳ ቴኒስ ጨዋታ ሊደረግ ታስቦ በዕለቱ ከባድ ዝናብ በመዝነቡ ምክንያት ሊሳካ አልቻለም።

የዕለቱ የክብር እንግዳ ብ/ጄኔራል ታዬ ጥላሁን (የመከላከያ ሚኒስተርና አምባሳደር የነበሩ) እና ኮሎኔል ሥምረት መድሃንዬ (የአየር ኃይልና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ) ወደ አዳራሹ ሲገቡ ፕሮግራሙ ተጀመረ። የመድረክ መሪው ታዋቂው የቀድሞው ሠራዊት ጋዜጠኛ ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ የእንኳን መጣቹህ ንግግር አድርገው፥ የኮ/ል ካሣ ገብረማርያምን ልጅ ዶ/ር ስንታየሁ ካሣን ወደመድረኩ ጋበዙ። እሷም የመታሰቢያውን ዕለት ለማክበር የመጡትን ሁሉ አመስግና ፕሮግራሙን ለኢትዮጵያ ልዓላዊነትና አንድነት መከበር መስዋዕት የሆኑትን የቀድሞ ሠራዊት አባላትን ሁሉ በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንዲያስታውሱ እንግዶቹን ሁሉ በመጋበዝ ንግግሯን ጀምራ በመቀጠልም ይህ ዕለት የሀዘንና የልቅሶ ሳይሆን በደስታ አባትዋን የመዘከሪያ መሆኑ፥ ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም ድንቅ የሆኑ የጦር መኮንን ብቻ ሳይሆን ፍቅር የሆኑ ሰው እንደነበሩም አስታውሳለች። በዚህም ወንድሟን አቶ እሸቱ ካሣ ወደ መድረኩ ጋብዛ፣ አቶ እሸቱም ይህ የመታሰቢያ በዓል በመደረጉ የተሰማውን ከፍተኛ ደስታና በአምላክ ፈቃድ መሆኑንም አስገንዝቦ ለዚህ ያበቃውን አምላክ በማመስገን ንግግሩን በአጭሩ አጠቃልሏል።

በዚህም የቁርስ ጊዜ ሆኖ እንግዶቹ የተዘጋጀውን ቁርስ ተጋብዘዋል። በመቀጠልም በሮራ ፀሊሙ ግዳጅ በመገናኛ ሠራተኝነት የተሳተፉና ከደብረ ማርቆስ ድረስ ለዚሁ በዓል ሲሉ የተገኙት አቶ ካሣ አበባየሁ በራሳቸው አነሳሺነት ስለ ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም የፃፉትን ልብ የሚነካ ድንቅ ግጥም ለታዳሚዎቹ አሰምተዋል።

ቀጥሎም ከ15 ዓመት በላይ አብረው በመሥራት ኮ/ል ካሣን በቅርብ የሚያቋቸው ብ/ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተማርያም በከፊል የሚያስታውሱትን በመግለጽ ንግግር ካደረጉ በኋላ ለብ/ጄኔራል ካሣዬ ጨመዳ መድረኩን ለቀዋል። ብ/ጄኔራል ካሣዬ ጨመዳ ደግሞ አጠርና ምጥን ያለ ልብና ወኔ የሚነካ ንግግር አድርገው ታዳሚውን አስደስተዋል።

ቀጣዬቹ ተናጋሪዎችም ኮሎኔል ካሣዬ ታደሰና ሻምበል ግርማ አስፋው ነበሩ። ኮ/ል ካሣዬ በልዩ ኃይልና በበረራ ደህንነት አብረው በመሥራት ኮ/ል ካሣን ያውቋቸዋል፥ ሻምበል አስፋው ደግሞ በሮራ ፀሊም ግዳጅ ተሳትፈው የመጨረሻውንም ሁኔታ ተመልክተው በተአምር የተረፉ ናቸው። ሁለቱም አጫጭር ምስክርነታቸውን በንግግር ገልጸዋል።

ሌላው ተናጋሪ ሻለቃ አርጋው ካብታሙ ነበሩ። ሻለቃ አርጋው በሐረር ጦር አካዳሚ በአስማሪነት ወቅትና ከኮ/ል ካሣ ገብረማርያም ቤተሰብ ጋርም ከነበራቸው ቅርበት አንፃር የሚያቁትን በመግለጽ ንግግር አድርገዋል። በልጃቸው በዶ/ር ስንታየሁ ካሣ የተጻፈውን የኮ/ል ካሣ ገብረማርያም የሕይወት ታሪክ የሚገልጸውን «ታሪክ የምትመሰክርልን ካሣ ገብረማርያም» የሚለውን መጽሐፍ አስመልክተውም አድናቆታቸውን ከገለጹ ወዲያ መጽሐፉ ስለ ኮሎኔል ካሣ የቀረው ነገር ይኖረው እንደሆን እንጂ የቀረበው ሁሉ እውነትነቱን በማረጋገጥ መስክረው ደምድመዋል።

ይህንን በዓል በአካል ተገኝቶ ክላርኔትና ሳክስፎን በመጫወት በሙዚቃ ያደመቀው አርቲስት ዳዊት ፍሬው፥ የታዋቂውና ዝነኛው አርቲስት ፍሬው ኃይሉ ልጅ ነበር።

ሌላው በተጋባዦች ቀርቶ በአዘጋጂዎቹ በኮ/ል ካሣ ገብረማርያም ቤተሰቦች ጭምር ያልተጠበቀና ያልታሰበ በዓሉን እጅግ ያደመቀና ያፈካው የኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር አባላት በኢትዮጵያ ባንዲራና የተለያዩ ሜዳሊያዎች አሸብርቀው በድንገት በበዓሉ መገኘት ነበር። ብዙዎቹ በዕድሜ የገፉ አባትና እናት አርበኞች ሲሆኑ ጥቂቶች ደግሞ በወላጆቻቸውን መዳሊያ ያሸበረቁ ወጣቶች ነበሩ። ታዳሚዎቹ ለአርበኞቹ ተገቢውን ክብር በጭብጭባና በሆታ ገልጸዋል። አንድ አባት አርበኛም አጭር ንግግር አድርገዋል። አርበኞቹ የመታሰቢያውን በዓል ከማድመቅ አልፈው ግርማና ሞገስ እንዳለበሱት አያጠራጥርም።

ይህንን የመታሰቢያ በዓል የምናከብርበትን ቀንና ቦታ በመግለጽ የሜዲያ ሽፋን እንዲያደርጉልን በማመልከቻ ለኢቢሲ፥ ለፋና፥ ለጄቲቪ፥ ለኤልቲቪ፥ ለሸገር ሬድዬና ለሌሎችም አስቀድመን አሳውቀን ነበር። ይሁንና ከኢሳት በስተቀር ሌሎቹ ሁሉ በዕለቱ አልተገኙም። ይህ ሁኔታም የዛሬ ሁለት ዓመት መጽሐፉን በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ስናስመርቅ በተመሳሳይ ሁኔታ ጥሪውን ቀድመን አድርሰን ያልተገኙልን መሆኑን እናስታውሳለን። የኮ/ል ካሣ ገብረማርያም አድናቂዎች የሆኑ ሁሉ ካሁን ቀደምም ለሜድያ ጥሪ እንዴት አላረጋችሁም የሚል ቅሬታ ያሰሙን ስለሆነ አሁንም ይህንን ቅሬታቸውን እንዳያነሱብን በኛ በኩል የሚጠበቅብንን መፈጸማችንን ለማስታወስ ያህል ነው እዚህ ላይ ያቀረብነው።

በሌላ በኩልም ለኢፌዲሪ የመከላከያ ሚኒስተር፥ ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለሲቪል አቪየሺን መሥሪያ ቤቶችም እንደዚሁ አሁንና ለመጽሐፉ ምረቃ ወቅትም በማመልከቻ ጥሪ ማድረሳችንን ማሳወቅ እንወዳለን።

በመጨረሻም ዶ/ር ስንታየሁ ካሣ በዕለቱ የሚገኘውን የመጽሐፍ ሽያጭ በሙሉ በአባቷ በኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም ስም ለበጎ አድራጎት ድርጅት ለመስጠት በገባችው ቃል መሠረት በዕለቱ የተገኘው የመጽሐፍ ሽያጭ 7 ሺ ብር፥ የክብር እንግዳ የሆኑት ብ/ጄኔራል ታዬ ጥላሁን ለዚሁ መልካም ተግባር የሰጡት 2 ሺ አምስት መቶ ብርና ከራሷ በመጨመር በጠቅላላው 30 ሺ ብር በሰበታ ከሚገኘው የመርሃ ዕውራን ት/ቤት አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጨርሰው የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመከታተል ለሚገኙት ተማሪዎች ለኑሯቸው መደጎሚያ እንዲሆን ሰጥታለች። በተጨማሪም ችግረኞች ለሆኑ የአርበኞች ማህበር አባላት ለዝግጅቱ አስተባብረው ባመጧቸው በልጅ ኤርሚያስ ተሰማና በተወካይዋ አሰተባባሪነት በአባቷ በኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም ስም የሚከፋፈል 10 ሺ ብር እርዳታ አበርክታለች።