ስለ መጽሐፉ አዘገጃጀት

ፀሐፊዋ የኮሎኔል ካሣ ገብረማርያምን ከልጅነት እስከ መጨረሻው ሕልፈታቸው ድረስ ያለውን ታሪካቸውን ለመጻፍ ከቤተሰብ፥ ከቅርብ ወዳጅና ጓደኞቻቸው፥ ከመጻሕፍት፥ መጽሔቶችና የመሳሰሉ ተጨባጭ መረጃዎች ሌላ ቁጥራቸው ከመቶ በላይ የሆነ በሕይወት የሚገኙና በቅርበት ከሚያቋቸው፥ በሰላም ሆነ በጦርነት አብረዋቸው ከነበሩና ከሠሩ፥ በሌላም መንገድ የተገናኟቸው የቀድሞ የመንግሥት ባለሥልጣኖች፥ የጦር መኮንኖች፥ የመሥሪያ ቤት ሃላፊዎች፥ አለቆቻቸውን፥ አቻዎቻቸውንና የበታቾቻቸውን አነጋግራለች። እነዚህም በአሜሪካ፥ በእንግሊዝ አገር፥ በጀርመን፥ በሌላ አፍሪካ አገርና በብዛትም በኢትዮጵያ የሚገኙ ናቸው። ከፊሉን በቅርበትና በአካል በመገናኘት፥ ከፊሉን በስልክና በሌላም የመገናኛ ዘዴ በመጠቀም ስታነጋግር፥ በጽሑፍም ምስክርነታቸውን የሰጡ ይገኙበታል።

ካነጋገረቻቸውም ውስጥ ሶስት ባለፈው መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች፥ ጥቂት ሚንስትሮችና አምባሳድሮች የነበሩ፥ 10 ሜ/ጄኔራሎች፥ 17 ብ/ጄኔራሎች፥ 32 ኮሎኔልች፥ብዙ ሻለቆችና ሻምበሎች እና ጥቂት ሲቪሎችም ይገኙበታል።

ቁልፍ የሆኑ ክንውኖችን እንደ ግዳጅና ጦርነት አይነቶችን በአካል ተገኝተው አብረው የተሳተፉ፥ የተካፈሉ፥ በደንብ የሚያውቁና አሁን በሕይወት የሚገኙ፥ በወቅቱ መሥመራዊ መኰንኖች የነበሩ መኮንኖች ምሥክርነታቸውን በማግኘት ታሪኩን አዳብራዋለች። መረጃዎችን ለማሰባሰብ እጅግ ጥራለች፤ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ድረስ በመሄድ በፈቃድ አንዱን የቀድሞ ባለሥልጣን ለማነጋገተር ስትበቃ፥ በሻዕቢያም በኩል ከመጻሕፍትና በሌላም መንገድ ካገኘችው መረጃ እና ማስረጃ ሌላ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩ ሰውን በማግኘት አነጋግራ ድንቅ  ምስክርነት አግኝታለች። ባጠቃላይም ጥናቱና ቃለ-ምልልሱ ረዥም ጊዜ ወስዶባታል።