ስለ ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም በአጭሩ፦

Col_KassaH1
ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም
  • በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ልዩ ኃይልን (ስፔሻል ፎርስ) አደራጅተው መርተዋል። እራሳቸው እየመሩ በሱማሊያ ድንበር በሚስጥር በመሥረግ ብዙ የኢትዮጵያ ሕዝብ የማያቃቸው ግዳጆችን በድል አጠናቅቀዋል። ይህም ሱማሊያ ኮማንዶዎቿዋን አሰርጋ በማስገባት ፈጥራብን የነበረውን የሰላም መደፍረስ የገታና አገሪቱንም ለሰላም ድርድር ያበቃ ድል ነበር።
  • የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሸባሪዎች ሲታወክ የበረራ ደህንነትን በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ፥ በዓለም አቀፍ ደረጃም ከእስራኤል ቀጥሎ፥ በመመሥረት መርተዋል። ያም የአየር መንገዱንና የአገራችን ክብር በዓለም አቀፍ መድረክ ያስጠበቀ ኃይል ነበር።
  • በአገሪቱ በነበሩት በሁለቱም የጦር ት/ቤቶች አስተምረው በአንዱ ለአዛዥነት በቅተዋል።
  • በሰሜን አንድ ግብረ ኃይል በመምራት ጀብሃና ሻዕቢያን በመዋጋት ብዙ መስዋዕትነት በመክፈል፥ ከትግራይ አሥመራ የሚስገቡትን መንገዶች ከፍተው አሥመራ በመግባት ለቀሪው የወገን ጦር የድል ጎህ አብርተዋል።
  • ናቅፋን ለማስለቀቅ በወጣው የውጊያ ዕቅድ በተሰጣቸው ልዩ ግዳጅ አንድ ንዑስ ግብረ ኃይልን መርተው በጠላት ወረዳ ሰንጥቀው በመግባት ግዳጃቸውን በሚገባ ተወጥተው ድል ካደረጉ ወዲያ በአቅርቦት፥ ድጋፍና ደጀን እጦት ገሚሱ ሠራዊታቸው በውሃ ጥም ሲፈታና ጠላት አንሰራራቶ ሲከበቡ እራሳቸውን በራሳቸው ለአገራቸውና ለወገናቸው በክብር መስዋዕት ያደረጉ ናቸው።
  • ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም ለአንድ የእግረኛ መኮንን የሚሰጠውን ኮርስ በአገርና በውጭ ያጠናቀቁ ናቸው። በአሜሪካ መሠረታዊ የመኮንኖች ኮርስ፣ ከፍተኛው የመኮንኖች ኮርስ እና የአዛዥነትና የመምሪያ ኮለጅ ኮርስ ወስደዋል። በተጨማሪም የሬንጀር ኮርስ፣ የአየር ወለድ ኮርስ፣ የመገናኛ ኮርስና የማመላለሻ መኪናዎች ጥገና ኮርስ በዚሁ በአሜሪካን አገር ተምረዋል። በዩጎዝላቪያም የስለላና ፀረ-ስለላ ኮርስ የተማሩ ሁለገብ የሆኑ መኮንን ነበሩ።