መጽሐፉ – “ታሪክ የምትመሰክርልን . . .” ካሣ ገብረማርያም ደራሲ – ስንታየሁ ካሣ
ግምገማ – በዶ/ር ሳህለሥላሴ ብርሃነ ማርያም (ደራሲ፥ ሃያሲ፥ ተርጓሚና የክብር ዶ/ር ናቸው።)
ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ/ም በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል

ኮ/ል ካሣ ገብረማርያምን አላቃቸውም።ይህንን መጽሐፍ እስከማነብ ድረስ ስለእሳቸው ሰምቼም አላውቅም ግን መጽሐፉን ለማንበብ እድል አገኘሁ። እና ስለዚህ መጽሐፍ በጣም አጭር የሆነ የተሰማኝን ምልከታ ለመናገር ነው የተጋበዝኩት። ስለተጋበዝኩም አመሰግናለሁ።
በመሠረቱ ይህ መጽሐፍ የሕይወት ታሪክ ነው። እና የሕይወት ታሪክ አጻጻፍ እስከዛሬ ድረስ የምናውቀው አብዛኛውን ጊዜ ባለታሪኩን ጠይቆ፥ ቃለ ምልል አድርጎ፥ ባለታሪኩ የጻፋቸው ማስታወሻዎች ካሉ ወይንም ደግሞ በሜድያ የሚገሩ ሌሎች ነገሮች ካሉ፥ ስለባለታሪኩ የተጻፉ መጻሕፍት እንዳሉ፥ ይህንን ሁሉ ፈትሾና የሚጽፈው ሰው ራሱ ምስክርነት ሰጥቶ እንደሚዘጋጅ ነው እስካሁን ድረስ አብዛኛው የምናውቀው። ይኸኛው ከተለመደው ትንሽ ለየት ያለ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ይኸውም በመሠረቱ ምንድነው ባለታሪኩን ጠይቆ ሳይሆን ባለታሪኩን የሚያቁ ሰዎች፥ የእሳቸው የበላይ የሆኑ አለቆቻቸው፥ ሌሎች በእሳቸው ሥር ያሉ ሰዎች፥ በሦስተኛ ደረጃ በአንድ መሥመር ያሉ የሥራ ባለደረቦቻቸው በመጠየቅ ነው። አብዛኞቹ ደግሞ የጦር ሰዎች ናቸው። እናም በቅርብ የሚያቋቸው ናቸው። ሲቪሎችም አልፎ-አልፎ እንዳሉ ነው የምገምተው። እና እነዚህ በቅርብ የሚያቋቸው ሰዎች ምሥክርነታቸውን ሰጥተዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን የመጽሐፉ ደራሲ፥ ዶ/ር ስንታየሁ፥ ስለሰዎቹ፥ ምስክር የሚሰጡ ሰዎች እራሳቸው ማን ናቸው? የሚታመኑ ናቸው ወይ? ከሚል አንጻር የእነሱንም መሠረታዊ ታሪክ ጭምር ነው የሰጠችን። አንቺ ስል ከዕድሜ አንጻር ነው፥ ከዶ/ር አንጻር አንቱ፥ ከመጽሐፉም አንጻር አንቱ ማለት ነበረብኝ። እና ታሪኩን የሚያቁ ሰዎች እራሳቸው ማን ናቸው የሚለውን ሁሉ አጠቃልላ ነው ያቀረበችው። ይህ ደግሞ ለመጽሐፉ ተአማኒነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብዬ እገምታለሁ።
በስሜታዊነት የተጻፈ አይደለም። ከቤተሰብ አንጻር፥ ከአባትና ልጅ አንጻር የተጻፈ አይደለም። ከወገናዊነት አንጻር የተጻፈ ኣይደለም። ተጨባጭ (ኦብጄክቲቭ) በሆነ መንገድ ጥርት ያለ ማስረጃ ከሰዎች፥ ከሚያውቋቸው ሰዎችጋ መረጃዎችን ሰብስበው ያቀረቡት ድንቅ የሆነ የሕይወት ታሪክ ነው ወይም ባዮግራፊ ነው።
ሁለተኛው ነጥብ ለማንሳት የምፈልገው ለመሆኑ ይህ መጽሐፍ የአንድ ሰው የሕይወት ታሪክ ብቻ ነው ወይስ ሌላ የሚያስፈልገን ነገር ይኖረዋል? የሚል ጥያቄ ለማንሳት ነው የምፈልገው። በእርግጥ መጽሐፉ የአንድ ሰው የሕይወት ታሪክ ነው። ነገር ግን ከሱ ጋር የተያያዙ የዘመናችንን ታሪክ የሚገልጹ ብዙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ እስከዛሬ ድረስ ብዙ መልስ ያላገኘ አንድ ጥያቄ እንዳለ አውቃለሁ። የደርግ መንግሥት ግዙፍ ኃይል ነበረው። እንደሚባለው እስከ 500ሺ ያህል ወታደር እንደነበረው ነው የምንሰማው። ነገር ግን በቁጥር በጣም አናሳ የሆነ የተገንጣዮች ቡድን አሸንፏል። እንዴት ሊሆን ቻለ? እኔ በበኩሌ እስከዛሬ ድረስ የተሟላ መልስ አላገኘሁም። አዛዦቹ ከታወቀ ሚሊቲሪ አካዳሚ የመጡ ናቸው። ወታደሮቹ በዘመናዊ መንገድ የሠለጠኑ ሰዎች ናቸው። እንዴት በነዚህ በጥቂት ተገንጣዮች ሊሸነፉ ቻሉ? ይህ መጽሐፍ ለዚህ ጥያቄ ሙሉ መልስ አይሰጥም። ነገር ግን አንዳንድ ፍንጮች እንዳሉ ነው የተገነዘብኩት። ለምሳሌ ከላይ አመራር ወደታች የሚተላለፉት ትዕዛዞች ሁልጊዜ ትክክል ነበሩ ወይ? ሆን ተብሎ የተደረገ አሻጥርስ ነበር ወይ? አዛዦቹ በሙሉ ነፃነት ወታደሮቻቸውን ያዙ ነበር ወይ? እና እንደዚህ የመሳሰሉ ብዙ-ብዙ ጥያቄዎች የሚያስነሱ ናቸው። ስለዚህ ለወደፊቱ የኢትዮጵያን ታሪክ፥ በተለይም የዘመናችንን ከ1966 ዓ/ም ወዲህ ያለውን ታሪክ ለመጻፍ የሚፈልጉ ባለሞያ የታሪክ ፀሐፊዎች እንደግብዓት ሊጠቀሙበት የሚችሉ መጽሐፍ ነው ብዬ እገምታለሁ። እና በአጠቃላይ ግን ዶ/ር ስንታየሁ ካሣ ለአባታቸው ግዙፍ የሆነ ሃውልት እንዳቆሙ ነው እኔ የምቆጥረውና ብናጨበጭብላቸው በጣም ደስ ይለኛል።