ልዩ ዝግጅት በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል

ከወራቶች በፊት ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያምን ለማስታወስና የመጽሐፍ ምረቃ ዝግጅቶች በአሜሪካን አገር በቬሪጂኒያና በዳላስ ከተሞች መደረጋቸው ይታወሳል። የአዲስ አበባው ዝግጅት ለኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም ቤተሰብ፥ የቅርብ ዘመድና ወዳጅ ሁሉ በብዙ መልኩ የተለየ ነበር። ከሁሉም በላይ እራሳቸውን ለወገንና አገር በሰውበት ምድር፥ በኢትዮጵያ፥ መታወሳቸውና የሕይወት ታሪካቸውም ለሕዝብ ለንባብ መብቃቱ እጅግ የሚያረካ በመሆኑ ነው። ስለሆነም ይህ ዝግጅት ከቤተሰብም ውጭ በብዙ ሰዎች በናፍቆትና በጉጉት ይጠበቅ የነበር ነው።

እንግዶች ቅዳሜ፥ ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ/ም፥ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምረው አዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ወደ ዝግጅቱ አዳራሽ ለመግባት ሲያመሩ በቀኝ በኩል ግድግዳውን ያለበሰው አንድ ግዙፍ የማስታወቂያ ሰሌዳ (ባነር) እና ወለሉን ያደመቀው የቀይ ምንጣፍ አይናቸውንና ኅሊናቸውን ይስበዋል። ሰሌዳው የመጽሐፉን ሽፋንና ልዩ-ልዩ ክፍሎችን የገዘፈ ምስል ይዟል፥ ምንጣፉ ሲታከልበት ፎቶግራፍ ለመነሳት የሚጋብዝ መድረክ ነበር!

ከታዳሚዎቹ ውስጥም የቀድሞው የኢፌድሪ ፕሬዝደንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ፥የቀድሞው መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች እንደ ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስና ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ፤ የቀድሞው ሠራዊት ብዙ ጄኔራሎች፥ ከፍተኛ እና ዝቅተኛ መኮንኖች፥የሠራዊቱ አባሎችና ከሲቪልም እንደዚሁ ከፍተኛ ባለሥልጣኖችና ታዋቂ እንግዶች ይገኙበታል።

የመድረኩ መሪ ሻለቃ አርጋው ካብታሙ ታዳሚዎቹ ጥሪውን አክብረው በመገኘታቸው የከበረ ምሥጋና በማቅረብ ዝግጅቱን ከፍተው፥ስለ ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም የአላቸውን የእራሳቸው ትውሳታ ተናግረው፥ የዝግጅቱን ፕሮግራም በአጭሩ አስተዋውቁና መድረኩን ለደራሲዋ ልጅ ካሣ ካሣሁን ለቀቁለት። እሱም አማርኛ አለመናገሩን ገልጾ ስለአያቱ ስለ ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም ከወላጆቹና ከወዳጅ ዘመድ ሲሰማ ማደጉን፥ አያቱ ድንቅ የሆነ ታሪክ ያላቸው ሰው መሆናቸውን ማወቁንና እናቱ ምን ያህል ደክማ መጽሐፉን ለንባብ እንዳበቃችው በመግለጽ በንባቡ እንዲረኩ ታዳሚዎችን ጋብዞ “አሁን ውብ እናቴን ወደመድረኩ እንድትመጣ እጋብዛለሁ!” በማለት ንግግሩን በአጭሩ ቋጭቶ ተሰናበተ።

ሻለቃ አርጋው ቀበል በማድረግ የደራሲዋን አጭር የሕይወት ታሪክ አሰምተው ወደ መድረኩ ጋበዟት። ደራሲዋ፥ ዶ/ር ስንታየሁ ካሣ፥በመጀመሪያ ለእንግዶቹ ታላቅ ምስጋና አቅርባ፥ ዕለቱን የሠርጓ ቀን ያህል ልዩ አድርጋ እንደወሰደችው እና በዚህ በያዝነው በሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ አባቷ ለአገራቸውና ለወገናቸው የተሰውበት ሰላሣ ስምንተኛው ዓመት መሆኑን ገለጸች። በመቀጠለም የመጽሐፉን አዘገጃጀት፥ በዝግጅቱ ሂደት የገጠሟትን አንዳንድ ስሜቷን የነኳትን ሁኔታዎች እና ከመጽሐፉም አንዳንድ የአባቷን ቀልዶች በማንሳት አጭር ንግግር አደረገች። ከዚያም ለመጽሐፉ ዝግጅት የረዷትንና የዕለቱን ዝግጅት ለማስተባበር የደከሙትን የኮሚቴ አባላት በሙሉና በጥቅሉ ከፍ ያለ ምሥጋና አቅርባላቸዋለች። ከመጽሐፉ ዝግጅት ብ/ጄኔራል ዋስይሁን ንጋቱን እና ከኮሚቴው አባላትም ውስጥ ካፒቴን ግዛቸው ወንድይራድን በስም በማንሳት የተለየ ምስጋና አቅርባላቸዋለች።

የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንግድ ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ስምረት መድሐንዬ የግል ፕሮግራማቸውን አዛብተው በዚሁ ዝግጅት ለመገኘት ሲሉ ከካናዳ ድረስ መምጣታቸውን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ደምሴ እጅጉ የዚህን ዝግጅት የሒልተን ሆቴል ወጪ ለመሸፈን ኣንድትፈቅድላቸው እንደጠየቋት አንስታ ይህም ሰዎች ለአባቷ ያላቸውን ከፍተኛ ፍቅር ማሳየቱን በመጥቀስ ሁለቱንም አመስግናቸዋለች። እናቷ ወ/ሮ አሰለፈች ኃይሌ መጽሐፉ ተገባድዶ ይህንን ቀን በጉጉት ሲጠብቁ በሕመም መለየታቸውን ጠቅሳ፤ በአሁኑ ሰዓት አባትና እናቷ በደስታና በኩራት እንደሚመለከቷት እርግጠኝነቷን ገልጻ ለእግዚአብሔር ልዩ ምስጋና አቅርባለች። በዚህም የኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም የሕይወት ታሪክ በአጭሩ የሚያሳየውን ስዕላዊ ትዕይንት(ስላይድ) እንዲመለከቱ ታዳሚዎችን በመጋበዝ ንግግሯን አጠቃልላች።

ትዕይቱ አልቆ፥ ቀጥለው የቀረቡት በደርግ ጊዜ ከፍተኛውን የጦር ሜዳ የጀግና ሜዳልያ የተሸለሙትና ከኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም ጋር በተለያዩ ክፍሎች አብረው ለረዥም ጊዜ የሠሩት ብ/ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተማርያም ናቸው። ብ/ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተማርያም  “ያልተነገረለት፥ ያልተዘፈነለት እና ያልተዘመረለት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያምን የማቃቸው ሻምበል ሆነው በ1957 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ህልፈተ ሞታቸው ጊዜ ድረስ ነው።” በማለት ንግግራቸውን ጀመሩ። ከዚያም 15 ዓመት ያህል አብረው መስራታቸውንና በጣም ፈታኝ፥ የሕይወት መስዋዕትነት የሚጠይቁ ብዙ ግዳጆችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አብረው መፈጸማቸውን ገልጸው፤ ኮሎኔል ካሣ በትምህርትና በልምድ ካካበቱት ወታደራዊ ሳይንስ ዕውቀታቸው፥በእስፓርት የዳበረ አካላቸው ሌላ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውና አገር ወዳድ ቆራጥ መኮንን እንደነበሩ አብራርተዋል። ከልዩ ተስጥኦቸውም ውስጥ በጦር ልምምድ ወቅት ከሠልጣኙ ጦር ጋር ከመጀመረያ እስከ መጨረሻ እንደ ተራ ሠልጣኝ ሆነው ኣብረው ሥልጠናውን መወጣታቸው፤ በጦር ሜዳም ትዕዛዝ ሰጥተው ቅደሙ ብለው ከኋላ መከተል ሳይሆን ቀድመው ተከተሉኝ የሚሉ እንደነበሩ መስክረዋል። ከዚያም ኮሎኔል ካሣ ለሠራዊቱ አዛዥ፥ አባት፥ ሞግዚት እና የቅርብ ጓደኛ ሆነው ሠራዊቱ ሲደሰት አብረው የሚደሰቱ፥ ሲያዝንም አብረው የሚያዝኑና ለሠራዊቱ ቤተሰብም የሚያስቡ፥ የሚያዝኑ፥ ቸር፥ የዋህና ርህሩህ አዛዥ እንደነበሩ ዘክረዋል። የኮ/ል ካሣን የአመራር ችሎታና የተለየ የአማራር ዘይቤአቸውንም በዝርዝር አስረድተዋል። የመጨረሻውን የኮ/ል ካሣን ግዳጅ አስመልክቶም በወቅቱ በቦታው ባይኖሩም ካገኙት መረጃ ተነስተው ገልጸውታል። በመጨረሻም የኮ/ል ካሣ ታሪክ ሰፊ መሆኑን አስታውሰው፥ ንግግራቸውን በጀመሩት መልክ «ያልተነገረላቸውና ያልተዘመረላቸው የኢትዮጵያ ልጅ ጀግና ኮሎኔል ካሣ ናቸው።ታሪክ ምንጊዜም ኮ/ል ካሣ ገብረማርያምን አይረሳቸውም። ሁልጊዜ ሲዘክራቸው ይኖራል!» በማለት ደምድመዋል።

ከዚያ በልዩ ኃይል እና በበረራ ደህንነት ከኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም ጋር የሠሩት ካፒቴን ግዛቸው ወንድይራድ ቀርበው በውጭ አገር በአንድ የምግብ ቤት ግድግዳ ላይ ሠፍሮ የተመለከቱትን “ታሪክ እና አገር አይሞትም” የሚለውን ጥቅስ አንስተው “ይህንን አሁን ልጃቸው ዶ/ር ስንታየሁ ካሣ የአንድ ሰው ታሪክ አለመሞቱን በመጽሐፉ አሳይታለች። በጣም የሚያስደስት ነው!” በማለት የኮ/ል ካሣን ታሪክ በሚገልጸው በዚህ መጽሐፍ ምረቃ ምንኛ መደሰታቸውን ገልጸዋል። ከዚያም ምንም ዓይነት የተለየ ሥልጠና እና ልምድ ሳይኖራቸው የመጀመሪያውን የበረራ ደህንነት ተግባር እንዴት በወኔና በአገር ፍቅር ብቻ በኮ/ል ካሣ መሪነት እሳቸውና ኮ/ል ካሣዬ ታደሰ ሆነው እንደጀመሩት አብራርተዋው ኮሎኔል ካሣዬ ታደሰን ከታዳሚዎቹ መሃል እንዲነሱ ጠይቀው ለሕዝቡ አስተዋውቀዋል።

ቀጣዩ ተናጋሪ ብ/ጄኔራል ካሣዬ ጨመዳም ሌላው የጀግና ሜዳሊያ ተሸላሚ ናቸው። “እዚህ የተሰበሰብነው ሁሉ የምንጋራው ነገር – ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም ቆራጥ፥ ጀግና፥ በወታደራዊ ሳይንስ እውቀታቸው አንቱ የተባሉ፥ መንፈሰ ጠንካራ፥ ከሁሉም በላይ አገራቸውን ከምንም በላይ የሚወዱ፥ደግ፥ርህሩህ፥ተግባቢና ተጫዋች ሰው መሆናቸው ነው።” በማለት ንግግራቸውን ጀምረዋል። ከዚያም መጽሐፉን ቀድመው ማንበባቸውን ጠቅሰው፥ የመጽሐፉን የመረጃ ምንጮች ከዘረዘሩ በኋላ ዶ/ር ስንታየሁ ካሣ በምንም መልኩ ሀቁን ከማስቀመጥ ውጭ በስሜት ወገንተኛ አለመሆናቸውን በግልጽ ማረጋገጡንና ይህም ለመጽሐፉ ክብደት እንደሚሰጠው እምነታቸውን ገልጸዋል።

የመጨረሻውን ዘመቻ አስመልክቶ በቅጡ አለመታቀዱን በደንብ ካብራሩ በኋላ እነዚያ ሦስት ቀደምት መኮንኖች እንደዚያ አንድላይ መመደባቸው ሌላ ተልዕኮ እንደነበረው ማሳየቱንና ዘመቻውን በበላይነት የመሩት ሰዎች አንድ ደባ የያዘና ነገር ያለበት እንደነበራቸው ማሳየቱን ገልጸዋል። “በመጨረሻም አንድ ሰው በሩቅ ርቀት በአጸደ ነብስ ይታየኛል። ቸር፥ ደግና ጀግና ሲሆን ‘አደራዬን ለእምዬ ኢትዮጵያ ተወጥቻለሁ’ ይለኛል። አዎን እኛም አክብሮታችንን፥ አድናቆታችንንና ምስጋናችንን እንገልጻለን። ይታየኛል ዛሬ መጽሐፉን የዘከርንውን ያህል ነገ በኢትዮጵያ ትንሳኤ ለካሣ የሚገባውን ነገር ዕድሜ ከሰጠን ቁጭ ብለን እናየዋለን።” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

ኮሎኔል ስምረት መድሃንዬ የቀድሞው የአየር ኃይል ቀደምት መኮንን፥ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የአየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ የነበሩና አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸው። በመጀመሪያ ያብራሩት የአውሮፕላን ጠለፋ እንዴት እና ለምን እንደተጀመረና የእስራኤል እና የኢትዮጵያ አየር መንገዶችም የመጀመሪያዎቹ ተጠቂዎች እንደነበሩ በማብራራትና በመግለጽ ነበር።  ወቅቱ እንኳንስ መሣሪያ ታጥቆ በአየር ላይ መከላከል ይቅርና በምድር መንገደኞችን ከመሳፈራቸው በፊት መፈተሹ እንኳን ተቀባይነት ያልነበረው እንደነበር አስታውሰዋል። የጠለፋ ደባ አለ ተብሎ የአየር መንገዱ አስተዳደር በከባድ ውጥረት ላይ በነበረበት ወቅት ኮ/ል ካሣ ገብረማርያም በበረራ ደህንነት አዛዥነት ተመድበው ሲመጡ እሳቸው ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንደነበሩ አስታውሰው፤ የተፈጠረውን ችግር ሲያማክሯቸው ኮ/ል ካሣ “ይህንን ለኔ ተውልኝ” በማለታቸው ያኔ ምን ያህል ከባድ ጫና ከላያቸው ላይ እንዳወረዱላቸው በማስታወስ ገልጸው ያንን የመጀመሪያውን ግዳጅም እንዴት በድፍረትና በወኔ እንተወጡት አብራርተዋል። ከዚያም ለብዙ ዓመታት ሲሠሩ ከጠላፊዎቹ በቀር በማንም መንገደኛ ወይም ሠራተኛ የሞት አደጋ ምንም ሳይደርስና በንብረትም ላይ ከባድ ጉዳት ሳይደርስ የአየር መንገዱን ጸጥታ መጠበቃቸው የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው ኮሎኔል ካሣና አብረዋቸው የሠሩትንም ሁሉ አመስግነዋል። በመጨረሻም እነ ካሣ የሠሩት ሥራ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቪየሽንም፥ በምሳሌነትም የሚታይ እንደነበር፥ የማይረሳ እና ሊረሳ የማይገባው ተግባር መሆኑንና መመስገንም እንደሚገባቸው በመግለጽ ደምድመዋል።

በቀድሞው ሠራዊት የመድፈኛ አባል ሆነው በኮ/ል ካሣ ገብረማርያም የመጨረሻው ግዳጅ ተካፍለው የመጨረሻውን ሁኔታ በዓይን ከመሰከሩት አንዱ የሆኑት ሻምበል ግርማ አስፋው ናቸው ቀጥለው መድረኩን የወሰዱት። በመጀመሪያም ደራሲዋ መጽሐፉን እዚህ ደረጃ ለማድረስ ያደረገችውን ከባድ ጥረት አድንቀው ክብርና ምስጋና ይገባታል ካሉ ወዲያ የዛሬ 38 ዓመት ከናቅፋ ቃሮራ የሚወስደውን መንገድ ለመዝጋት በተሰጣቸው ግዳጅ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዛዡ ከኮ/ል ካሣ ጋር መገናኘታቸውንም አስታውሰዋል። ሠራዊቱ ሲጀመር ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ቦታዎች እየተቆጣጠረ በድል ወደ ሮራ ፀሊም አምርቶ በመጨረሻም ስትራተጂካዊ ቦታዎችንና ከሁሉም በላይ የውሃ ነጥቡን እንደያዘ ገልጸው ከዚያ ሠራዊቱ የውሃ ነጥቡን ለቆ ወደፊት እንዲንቀሳቀስ ከበላይ አካል ትዕዛዝ ለአዛዡ ለኮ/ል ካሣ መሰጠቱንና እሳቸውም የውሃ ነጥቡን መልቀቅ በወገን ጦር ላይ የሚያመጣውን ውድቀት በመግለጽ መከራከራቸውንና በመጨረሻም አንዳልሆነ መስክረዋል። ከዚያም ወዲያው ጦሩ ወደፊት እንዲንቀሳቀስ አዛዡ ትዕዛዝ መስጠታቸውንና ችግር እንዳለ ሁሉም ቢረዳም የበላይ አካል ትዕዛዝ ለመፈጸም ሲባል ብቻ እንቅስቃሴው ተደረገ ብለዋል። ይሁን እንጂ የተፈራው ነገር መድረሱ እንዳልቀረና ጠላት የውሃ ነጥቡን ተቆጣጥሮ ማጥቃቱን እንደቀጠለ፤ በወገን ላይ ጥፋቱን እንዳፋፋመም ዘክረዋል። መድፎችና ሌሎችም የርቀት ማጥቂያ ከባድ መሣሪያዎች ከርቀት ውጭ በመሆናቸው ድጋፍ ሊሰጡ እንዳልቻሉና የወገን ጉዳት እየጨመረ እንደመጣ፥ ይልቁንም በውሃ ጥም የተጎዳው የሠራዊቱ ቁጥር የበዛ እንደነበር አስታውሰዋል። የሚከፈለው መስዋዕትነት እየጨመረ ቢሄድም ለወገን የሚደርስለት ምንም ኃይል እንዳልነበር ገልጸዋል። ያ ጠላትን ሲያርበደብድ የነበረ ወኔ የተሞላበት ወጣት ተዋጊ በውሃ ጥም ተዝረክርኮ አቅም እንደአነሰውና ሁኔታውም ማንም ሠራዊት ሊቋቋመው ከሚችለው በላይ በመድረሱ ያንን ሁኔታ የተመለከቱት ኮሎኔል ካሣ የእነዚህን ወታደሮች ዕጣ ፈንታ ከማይና በጠላት እጅ ከምወድቅ በማለት በጀግንነት እራሳቸውን በታጠቁት መሣሪያ መስዋዕት እንደአደረጉና አብረዋቸው የነበሩ እነ ሌ/ኮሎኔል ሠይፉ እና ሌሎች መኮንኖችም እራሳቸውን እንደሰው መስክረዋል።  “የመቅደላው ካሣ – ቴዎድሮስን ምሳሌ በመጠቀም የሮራ ፀሊም ካሣ ገብረማርያም ሽጉጣቸውን ጠጥተው ለአገራቸው ክብርና ሰንደቅ በክብር አረፉ።” በማለት ደግመው የተመለከቱትን አረጋግጠው፤ “ክብርና ሞገስ ለጀግኖቻችን!” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

ከዚህ በመቀጠል የቀድሞው ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ በጣም አጭር የሆነ ንግግር አድርገው ዝግጅቱ ወደ የመጽሐፍ ግምገማ ክፍለ ጊዜ ተሸጋገረ። በመጀመሪያ የዶ/ር ሳህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም ግምገማ ተሰምቶ ወዲያው በአቶ ዘነበ ኦላ ግምገማ ተተክቷል። በንግግር የቀረቡትን ግምገማዎች በጽሁፍ ለብቻ አቅርበናልና በስማቸው ያቀረብነውን ማስተሳሰሪያ (ሊንክ) በመጫን እንድታነቡ እንጋብዛለን።

ከመጽሐፍ ገምጋሚዎች ንግግር በኋላ የመድረክ መሪው ታዳሚዎች ለደራሲዋ ወይም ለመጽሐፍ ገምጋሚዎች የሚያቀርቡት ጥያቄ ካላቸው ወይንም አስተያየት መስጠት የሚሹ ከሆነ መድረኩ ክፍት መሆኑን ገለጹ። በዚህም ከታዳሚዎች መሃል እነ ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ እና ካፒቴን ግዛቸው ወንድይራድ አስተያየት ሲሰጡ፤ ብ/ጄኔራል ዋስይሁን ንጋቱ በዚህ ዝግጅት የአሜሪካና የካናዳ ኤምባሲዎች ወታደራዊ ልዑካንም መገኘታቸውን ገልጸው በስም ካስተዋወቋቸው በኋላ በዝግጅቱ በመገኘታቸውም ከፍ ያለ ምሥጋና አቅርበውላቸዋል። በዚህም የአዳራሹ ዝግጅት መፈጸሚያ ሆኖ እንግዶች የቡናና የሻይ ጊዜና ደራሲዋም መጽሐፍ የመፈረሚያዋ ወቅት መሆኑ ተገልጾላቸው ወደ መዝናኛው ሥፍራ አምርተው እጅግ በደመቀ ሁኔታ ዝግጅቱ ተከናውኗል። በአንዳንድ ሰዎች አስተያየት እንደዚህ ብዙ የቀድሞው መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች፥ የቀድሞው ሠራዊት ከፍተኛና ዝቅተኛ መኮንኖችና የሠራዊት አባሎች የተገኙበት የመጽሐፍ ምረቃ እስካሁን ድረስ ተደርጎ አያውቅም። ይህም የቀድሞው ሠራዊት ለኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም ያለውን ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት አድምቆና አጉልቶ ማሳየቱ ግልጽ ነው።